ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድነታችንና የጽናታችን ምልክት ነው  

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን እውን የሆነ የአንድነታችንና የጽናታችን ማሳያ ምልክት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባልና ተተኪ አርበኞች ገለጹ። 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አባት አርበኞች እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ያሳየ የአይችሉም መንፈስን የሰበረ ፕሮጀክት ነው።

እንዲሁም ከአባት አርበኞች የተወረሰው አይበገሬነትና ጽናት ማሳያ መሆኑን  ተናግረዋል።

የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባልና ተተኪ አርበኛ ትዕግስት ሃይሌ እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በልጆቿ ታሪክ የሰራችበት ፕሮጀክት ነው፡፡ 

አገር ተረካቢ ትውልድም መንግስት በዘረጋው ምቹ የልማት መስክ በመሰማራት አዳዲስ ታሪክ ሊሰራና ሊያስቀምጥ ይገባዋል ብለዋል።


 

በይቻላል መንፈስ እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ኩራት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ተተኪ አርበኛ አስማማው መከተ ናቸው።

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ብርታት ሳትደፈር መቆየቷን በማስታወስ፤ ወጣቱ ትውልድ አንድነትን ከአባቶቹና ከእናቶቹ በመማር የአገሩን ሉዓላዊነት በሁሉም መስክ ማስጠበቅ ይኖርበታል ብለዋል።

የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የአርበኛ ልጅና ተተኪ አርበኛ ሰብለ ንጋቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለዓለም የሚተርፉ ተተኪ ጀግኖችን የምታፈራና ለዓለም ምሳሌ የምትሆን አገር ናት።


 

ወጣቱ ትውልድ ቀጣይነት ያለው ተግባር  የሚሰራ መሆኑን በመጥቀስ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን የዚህ ትውልድ አርበኝነት መገለጫ መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው፤ ትውልዱ ዛሬ ላይ ቆሞ ነገን ማሰብ የቻለ፣ የወገኑንና የአገሩ ክብርና ጥቅም ለማስከበር ቀድሞ የነቃ ነው ብለዋል።

ትውልዱ የትላንቱን በመመርመር ስለነገ በማሰብ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን ማድረግ የቻለና ዓለምን ያስደነቀ ተግባር ለመፈጸም የበቃ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሆኑ ትውልዱ ዳግም ታሪኩን መሰረት በማድረግ መሰል ተግባራትን ሊያጠናክር እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል።

ከዓድዋ ታሪክ አንድነትን፣ ሕብረትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምንና ጽናትን መማር እንደምንችል አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም