የኢትዮጵያውያን ጽናትና ጀግንነት ከቀደሙት አያቶች የወረስነውና አሁንም ያስቀጠልነው መለያ ተግባራችን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያውያን ጽናትና ጀግንነት ከቀደሙት አያቶች የወረስነውና አሁንም ያስቀጠልነው መለያ ተግባራችን ነው
ጎንደር/ ደብረ ብርሃን / ደሴ ፤ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያውያን ጽናትና ጀግንነት ከቀደሙት አያቶች የወረስነውና አሁንም ያስቀጠልነው መለያ ተግባራችን ነው ሲሉ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምእራብ እዝ የ105ኛ ኮር የጠቅላላ አገልግሎት ሃላፊ ኮሎኔል አባይ በላቸው ገለጹ።
ጳጉሜን 1 "የፅናት ቀን" በጎንደር ፣ በደብረ ብርሃን እና በደሴ ከተሞች ፤ "ፅኑ መሰረት ብርቱ ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ በመከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ አባላት ወታደራዊ ትርኢት ተከብሯል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የሰሜን ምእራብ እዝ የ105ኛ ኮር የጠቅላላ አገልግሎት ሃላፊ ኮሎኔል አባይ በላቸው፤ የኢትዮጵያውያን ጽናትና ጀግንነት ከቀደሙት አያቶች የወረስነውና አሁንም ያስቀጠልነው መለያ ተግባራችን ነው ብለዋል።
በርካታ ጫናዎችንና ፈተናዎችን በማለፍ በጽናት የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ተናግረው የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት የማስጠበቅ፣ ልማቷን የማሰቀጠል ስራችን ይቀጥላል ብለዋል።
የሰሜን ምእራብ እዝ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሬጅመንት አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ ገብረወሃድ እና የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሰው ሃይል ልማት አዛዥ ኮማንደር አያል ተገኘ፤ በኢትዮጵያዊያን ፅናትና ጀግንነት ብዙ ነገሮችን አሳክተናል ተጠናክሮም ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ አለልኝ አለም በበኩላቸው የጽናት ቀን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ጽናት ያሳካቻቸውን ተጨባጭ ውጤቶች የምናወሳበት እና ቀጣይ ለሚያጋጥሙን ፈተናዎችም የላቀ ዝግጁነት የምንሰንቅበት ነው ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማም ጳጉሜን 1 "የጽናት ቀን" በተመሳሳይ የመከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ አባላት ወታደራዊ ትርኢት ተከብሯል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ደጀኔ ልመንህ፤ ሰላማችንን በማፅናት ልማታችንን በማስቀጠል የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እናስቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በበኩላቸው ጽናት የሉአላዊነታችን ማረጋገጫ ዋስትና በመሆኑ በእለቱ የክልሉን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ቃል የምንገባበት ነው" ብለዋል።
በሌላ በኩል የደሴ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አባላት የፅናት ቀንን ባከበሩበት ወቅት ከፀጥታ አባላት መካከል ሳጅን ዘውዱ በላይ እንደገለጹት፤ ከህብረተሰቡ ጋር ሰላም መጠበቃቸው በከተማው የተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
አሁን ያለውን ሰላም በማጽናት የተጀመሩ ልማቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማንኛውንም መስዋት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብሏል።
ኮንስታብል ሲሳይ ጌታቸው በበኩሏ፤ ፅናት ህዝብና የፀጥታ አባላትን ያበረታል፣ ሀገርንም ያሻግራል" ብላለች
የከተማችንን ሰላም ለማስቀጠል፣ ልማቱን ለማጠናከር በርትተን እንሰራለን ስትል ገልጻለች።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ከማንደር ሰይድ ዓሊ፤ የከተማው ፀጥታ አባላት የከተማውን ሰላም በመጠበቅ ልማቱ እንዲቀጥል ማስቻላቸውን ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ አመራሮች፣ የተለያዩ የፀጥታ አባላትና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።