ቀጥታ፡

በትምህርት ለትውልድ የሚሰጠው የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ተማሪዎች ተጨማሪ ዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ እያስቻለ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ)፦ በትምህርት ለትውልድ ብሔራዊ ንቅናቄ የሚሰጠው የክረምት ወራት የማጠናከሪያ ትምህርት ተማሪዎች ተጨማሪ ዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ እያስቻለ መሆኑን የትምህርት ቤት ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።

በኢትዮጵያ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በትምህርት ለትውልድ ብሔራዊ ንቅናቄ የትምህርት ጥራትን የሚያሻሻሉ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የትምህርት ለትውልድ ብሔራዊ ንቅናቄ መርሃ ግብርም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት ዕውቀትና ክህሎት የሚሸምቱበትን ከባቢን ፈጥሯል።

በብሔራዊ ንቅናቄው በክረምት ወራት የሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርትም ተማሪዎች ዕውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉ በማስቻል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች በንቅናቄው የተከናወኑ ስኬታማ ተግባራትም በምገባ፣ በክረምት ማጠናከሪያ ትምህርትና በሌሎች ጉዳዮች ተማሪዎችን ተጠቃሚ አድርጓል።

በትምህርት ለትውልድ ብሔራዊ ንቅናቄ በአዲስ አበባ የተከናወኑ ተግባራትን አስምልክቶም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከትምህርት ማህበረሰብ አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል።

በብርሃነ ህሊና 1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ ተወካይ ሀጂ ሲራጅ እድሪስ÷ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ ማጠናከሪያ ትምህርት ተማሪዎች ተጨማሪ ዕውቀትና ክህሎት እያስገኘላቸው ነው ብለዋል።

ተማሪዎች በክረምት ወራት የሚያገኙት የትምህርት ዕድልም በበጋ ወራት በመደበኛ ትምህርት የነበሩባቸውን የትምህርት ክፍተት በመሙላት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዳግማዊ ምኒሊክ ቅድመ 1ኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ ተወካይ ወንዱ አለማየሁ÷ የክረምት ወራት የማጠናከሪ ትምህርት ተማሪዎች ለሚቀጥለው የትምህርት ዘመን እንዲዘጋጁ እያገዘ ነው ብለዋል።

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በትምህርት ቤቶች የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማነትም የተመናሪዎች፣ የወላጆችና የማህበረሰቡ ትብብር ጉለህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

የ'ኒው ኤራ' የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ኤፍራታ ታምሩ÷ በክረምት ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት ውጤታችን እያሻሻለ ነው ብላለች።

የ'ኒው ኤራ' የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ዩናታል ወልዳይ÷ የማጠናከሪያ ትምህርቱ ቀጣይ ዓመት ለሚወስዱት የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንድንዘጋጁ በማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጣቸው መሆኑን ገልጿል።

የዳግማዊ ምኒሊክ ቅድመ አንደኛና መካከለኛ  ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናደው ባዩ÷ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ተማሪዎች የተሻለ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ እያደረገ ነው ብለዋል።

የትምህርት ማህበረሰቡም ትምህርት ቤቱ የተሻለ የመማር ማስተማር ምህዳር እንዲፈጠር በማስቻል ተማሪዎች ምቹ ዕውቀትና ክህሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ እንደፈጠረ ገልጸዋል።

የ'ኒው ኤራ' የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ትምህርት ቤት መምህር መምህር ያሬድ ብርሃኑ÷ በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ የትምህርት አገልግሎቶች የሚሰሩ ስራዎች ተማሪዎችን እያበቃ መሆኑን ተናግረዋል።

የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ ማጠናከሪያ ትምህርቱም ተማሪዎችን ለቀጣይ የትምህርት ዘመን በማዘጋጀት የተወዳዳሪነት አቅማቸውን በማሳደግ እገዛ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)÷ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ትምህርት ቤቶች ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢ እንዲኖራቸው አድርጓል ብለዋል። 

በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመንም 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ሃብት በማሰባሰብ ትምህርት ቤቶችን በማዘመን ስኬታማ የአሰራርና የአደረጃጀት ስርዓት እንዲፈጠር መደረጉን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም