በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባ ከተማ ያለማቋረጥ ወደ ፊት ይገሰግሳል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባ ከተማ ያለማቋረጥ ወደ ፊት ይገሰግሳል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ)፦ በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባ ከተማ ያለማቋረጥ ወደ ፊት ይገሰግሳል ፤ የትኛውም ምድራዊ ሀይል ካለመበት አያስቀረውም ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ ዛሬ የሚታሰበው ጳጉሜን 1 - የፅናት ቀን "ፅኑ መሠረት ብርቱ ሀገር" በሚል አገራዊ መሪ ቃል እንደሚከበር ገልጸዋል።
መሪ ቃሉም በፅናት ላይ የተገነባ ሀገር ጠንካራ እና ለየትኛውም ጊዜያዊ ፈተና የማይበገር፣ እጅ የማይሰጥ በመጨረሻም ድል አድራጊ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ፅናት ለእኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ቡናችን፣ እንደ ዓባይ ወንዛችን አንዱ መገለጫችን ነው ያሉት ከንቲባዋ በጦርነት አውድማ ቀደምቶቻችን በዓድዋ፣ በማይጨው፣ አትሌቶቻችን ደግም በስፖርት ሜዳ ፅናትን አሳይተውናል ሲሉ ገልጸዋል።
የቅርቡን እንኳን ብንመለከት በሕዳሴ ግድባችን የባዳ እና ባንዳው ጥምረት እንዳለ ሆኖ ለ13 ጊዜ ያህል በፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ስንሆን፣ ከውስጥም ከውጪም የተቀናጁ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን ዛሬ ግድባችንን ጨርሰን የደረስንበት የታሪክ እጥፋት ከመሪ እስከ ሕዝብ ያለንን ፅናት ለዓለም ሕዝብ ያሳየንበት ነው ብለዋል።
በስንዴ አብዮት፣ በአረንጓዴ አሻራ ጭምር የስኬታችን ዋነኛው ምሥጢር የመሪዎቻችን እና መሪውን የተከተለው ሕዝብ ፅናት ነው ሲሉም አክለዋል።
በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባ ከተማ ያለማቋረጥ ወደ ፊት ይገሰግሳል፤ የትኛውም ምድራዊ ኃይል ካለመበት አያስቀረውም፣ በአዲስ ኃይል አዳዲስ ስኬቶችን ይጨብጣል ብለዋል ከንቲባ አዳነች።
በከተማችን በ2017 ዓ.ም የታየው፣ ዓለምን ያስደነቀው፣ አዲስ አበባን አዲስ እና አበባ ያደረገው ሥር ነቀል መልሶ ማልማት፣ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት፣ የገቢ አሰባሰብ፣ የሰላም እና ፀጥታ ወዘተ በርካታ ተግባራት፣ እንዲሁ በቀላሉ የተገኘ ውጤት አይደለም፤ ይልቁኑ በፅናት በመጓዝ የተገኘ ነው ብለዋል።
ፈተና ሳይኖር ቀርቶ አይደለም፣ በሚሊዮን የሚቆጠር የከተማችን ነዋሪ ተሳትፎ፣ በፅናት የተቀናጀ የአመራር ሰጪነት የታየበት ተጨባጭ ውጤት፣ የጠንካራ ፅናታችን ውጤት በመሆኑ በአዲሱ የ2018 ዓመትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።
በዛሬው ዕለት የፅናት ቀንን ስናከብርም ለሀገራችን እና ለከተማችን ሁለንተናዊ ብልጽግና እንደ ከዚህ ቀደሙ የትኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ያለንን የማይናወጥ ፅናት ዳግም በማረጋገጥ መሆን ይኖርበታል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።