የአዲስ ዓመት የኪነጥበብ ስራው የሁለቱን ሀገራት የባህል ትስስር የሚያጠናክር ነው -አምባሳደር ኤርቨን ማሲንጋ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ ዓመት የኪነጥበብ ስራው የሁለቱን ሀገራት የባህል ትስስር የሚያጠናክር ነው -አምባሳደር ኤርቨን ማሲንጋ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በአሜሪካ ኤምባሲ ያቀረቡት የአዲስ ዓመት የኪነጥበብ ስራ የሁለቱን ሀገራት የባህል ትስስር እንደሚያጠናክረው ተገለጸ።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቨን ማሲንጋ መጪውን የኢትዮጵያውያን የ2018 ዓ.ም አዲስ አመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት አስመልክቶም የራስ ቴአትር የኪነጥበብ ሙያተኞች በአሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ባህላዊ ትርኢት አቅርበዋል።
በዚሁ ወቅት አምባሳደር ኤርቨን ማሲንጋ ኢትዮጵያውያን የአዲስ አመት በዓላቸውን በደማቅ ባህላዊ ስርዓት ሲቀበሉ ማየት ያስደስታል ብለዋል።
በአሜሪካ ህዝብና መንግስት ስም ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት በማስተላለፋቸው የተሰማቸውን ደስታ እና ኩራት ገልጸዋል።
የራስ ቴአትር የኪነጥበብ ሙያተኞች በአሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ላቀረቡት የኢትዮጵያዊያን ውብ ባህላዊ የኪነጥበብ ትርኢት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኪነጥበብ ሙያተኞቹ ያቀረቡት በህብረ ቀለማት እና ዜማዎች አሸብርቀው የቀረቡ ባህላዊ ትርኢቶች በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የባህልና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን መጪውን አዲስ አመታቸውን በአብሮነት እና በብሩህ ተስፋ እንዲቀበሉትም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
አዲሱ አመት የሁለቱ አገራት ጠንካራ ወዳጅነት ተጠናክሮ የሚቀጥልበት መሆኑንም ተናግረዋል።
አሜሪካም ኢትዮጵያ የብልጽግና ተስፋዋን ለማሳካት በምታደርገው ጥረት አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ነብዩ ተድላ በበኩላቸው ኢትዮጵያና አሜሪካ የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።
የራስ ቴአትር የኪነጥበብ ሙያተኞች በአሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ያቀረቡት ውብ ባህላዊ ትርኢትም የሀገራቱን ወዳጅነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመታቸውን ደስታን የሚጋሩበት እና በረከትን የሚመኙበት መሆኑን አስረድተዋል።
በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያም የአሜሪካ ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
#Ethiopian_News_Agency
#ኢዜአ
#Ethiopia
#ኢትዮጵያ