ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በምክክር ችግሮችን በመፍታት እጅ ለእጅ ተያይዞና ልብ ለልብ ተገናኝቶ መጓዝ ይገባል-ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም

መቀሌ፤ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በምክክር ችግሮችን በመፍታት እጅ ለእጅ ተያይዞና ልብ ለልብ ተገናኝቶ መጓዝ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል በመገኘት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች የተሳተፉበት የቅድመ ምክክር መድረክ በመቀሌ አካሄዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም፥ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በምክክር ችግሮችን በመፍታት እጅ ለእጅ ተያይዞና ልብ ለልብ ተገናኝቶ መጓዝ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም በሀገራዊ ምክክሩ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በምክክር ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ይገባል ብለዋል።

በዚህም መሰረት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የቅድመ ምክክር መድረክ ለዚሁ ስኬት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑን ገልፀዋል።

ለችግሮች ሁሉ ቁልፉ መፍትሄ ምክክር በመሆኑ እድሉን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።

የመድረኩ ተሳተፊዎችም ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር በዘላቂነት ለመፍታት ዝግጁ ስለመሆናቸው ማረጋገጣቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፥ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት ለመጀመርና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ቀደም ሲል ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ውይይት መደረጉን መግለፃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም