ቀጥታ፡

በኮፕ-30 የአየር ንብረት ጉባኤ የአፍሪካን ቀዳሚ አጀንዳዎች የሚያንጸባርቁ የድርድር ሃሳቦችን እናቀርባለን-ተደራዳሪ ቡድኑ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡-በብራዚል በሚካሄደው ኮፕ-30 የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ የአፍሪካን ቀዳሚ የልማት አጀንዳዎች የሚያንጸባርቁ የድርድር ሃሳቦችን ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን የአፍሪካ የአየር ንብረት ድርድር ቡድን ሊቀመንበር ሪቻርድ ሙዩንጊ(ዶ/ር) አስታወቁ።

13ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥና ልማት ጉባኤ ’’በሳይንስ፣ በገንዘብና በፍትሐዊ ሽግግር የአፍሪካን የአየር ንብረት እርምጃ ማንቃት” በሚል መሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ አፍሪካ ልማት ባንክና የፓን አፍሪካ የአየር ንብረት ፍትሕ ጥምረት የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ እስከ ጳጉሜን 2/2017 ዓ.ም ይቆያል።

በአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ አካባቢ ክፍል የዘላቂ አካባቢ ዲቪዥን ሃላፊ ጂሃኔ ኤል ጋዑዚ (ዶ/ር)፥ ጉባኤው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አየር ንብረት ሁነቶች የተሞክሮ ልውውጥ የሚደረግበት ነው ብለዋል።

በዚህም የአፍሪካን የአረንጓዴ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ማዕከል ለማድረግ የተሻሉ ዕድሎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስም የፋይናንስ አቅሞችን በማሳደግ የቴክኖሎጂና ሀገር በቀል የምርምር ስራዎችን ለማስፋት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ብቻ ሳትሆን የተጨባጭ መፍትሔዎች፣ የአመራር ብቃትና የተሻለ ተስፋ ያላት አህጉር መሆኗንም አንስተዋል።

የአፍሪካ የአየር ንብረት ድርድር ቡድን ሊቀመንበር ሪቻርድ ሙዩንጊ(ዶ/ር)÷ ጉባኤው አፍሪካ በአየር ንብረት ጉዳይ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ የምትገነባበት ነው ብለዋል።

በብራዚል ቤሌም እ.አ.አ. ከኅዳር 10 እስከ 21/2025 በሚካሄደው ኮፕ-30 የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ ቅድሚያ የምትሰጣቸው የልማት ግቦች እንደሚንጸባረቁ ገልጸዋል።

በጉባኤው የአፍሪካን የልማት መሻት ያነገቡ የተቀናጁ፣ ወጥነትና ጥራት ያላቸው የድርድር ሀሳቦች ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።

የአፍሪካን የልማት ጸጋዎች የዓለም አቀፍ የመፍትሔ ለማድረግ በአዲስ አስተሳሰብ ከቃል የዘለለ በመተባበር ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የፓን አፍሪካ የአየር ንብረት ፍትህ ጥምረት ፕሮግራሞች እና ምርምሮች ኃላፊ ቻርለስ ምዋንጊ (ዶ/ር)÷ በአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ለአህጉሪቱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል ግልጽ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።

አፍሪካ በ2030 የአየር ንብረት ግቦቿን ለማሳካት ከሚያስፈልጋትና ቃል ከተገባው ውስጥ ከ3 እስከ 4 በመቶ የማይበልጥ የፋይናንስ ድጋፍ እየተደረገላት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በብራዚል ቤሌም ከተማ በሚካሄደው ኮፕ-30 ጉባኤ ላይ የአፍሪካን የፋይናንስ ፍትሐዊ አጀንዳ በአንድ አህጉራዊ ድምጽ ማሰማት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም