የጽናት ቀን በፀጥታና ደህንነት መስኮች የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ስኬቶችን በሚያንጸባርቁ ዝግጅቶች ይከበራል - ኢንጂነር አይሻ መሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
የጽናት ቀን በፀጥታና ደህንነት መስኮች የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ስኬቶችን በሚያንጸባርቁ ዝግጅቶች ይከበራል - ኢንጂነር አይሻ መሐመድ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፦ ጳጉሜን 1 የጽናት ቀን በፀጥታና ደህንነት መስኮች የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ስኬቶችን በሚያንጸባርቁ ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበር የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ አስታወቁ።
ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ የጽናት ቀንን "ጽኑ መሠረት ብርቱ ሀገር" በሚል መሪ ሐሳብ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በዓሉ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እንደሚከበር ጠቁመው፤ ልዩ ልዩ የጥበብ ስራዎች፣ "የጽናት ሸማኔዎቹ" የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም፣ ዲጅታል አውደ ርዕይን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የፅናትን ሀገራዊ ዋጋ የሚያስገነዝቡ መርሃ-ግብሮች እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።
ዝግጅቶቹ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረች ባለችበት ወቅት የፀጥታና ደህንነት ተቋሞቿን ለማዘመን የሄደችበት ርቀት፣ የተመዘገቡ አስደናቂ ስኬቶች የጽናት መገለጫ ሆነው የሚቀርቡበት መሆኑን አመልክተዋል።
የጽናት ቀን የስኬትና የድል መሰረት የሆነውን ህዝባችንን የምናወድስበት ፣ በፀጥታና ደህንነት መስኮች የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ስኬቶች ዋጋ የሚሰጥበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በጽናት መቆማችንን የምናውጀበት፣ ኢትዮጵያውያን በማያወላዳ ቁርጠኝነት እና አንድነት ሀገራችንን ወደ ላቀ የብልፅግና ከፍታ ላይ ለማድረስ የሚያስችለንን የጽናት መንፈስ የምናድስበትም ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።
በነገው ዕለት ከረፋዱ 5:30 ላይ ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር በማሰማት በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ለቀጣይ ምዕራፍ የጽናት ጉዞ ቃል የሚገቡበት መርሃ ግብር እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የፀጥታና ደህንነት አካላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙም ጠቁመዋል።