የኪን-ኢትዮጵያ ጉዞ ቀጣይነት ያለው የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኪን-ኢትዮጵያ ጉዞ ቀጣይነት ያለው የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡-ኪን-ኢትዮጵያ የጥበብና ባህል ጉዞ ቀጣይነት ያለው የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥን ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ።
በሩሲያ የሚደረገውን ሁለተኛው ዙር ኪን-ኢትዮጵያ "የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት" የጥበብና ባህል ጉዞን በተመለከተ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከሻኩራ ፕሮዳክሽን ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እንዳሉት፥ የኪን ኢትዮጵያ ጉዞ ኢትዮጵያን በልኳ ለአለም ለማስተዋወቅ ያለመ ነው።
በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አስፈላጊ ከሆኑት መካከል አንዱ ኪነጥበብ መሆኑን ጠቅሰው፥ የኪን ኢትዮጵያ ጉዞ የኢትዮጵያን መልክ ለዓለም ለማሳየት ትልቅ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት፣ በርካታ ባህልና እሴት ያላት እንዲሁም የነፃነት ታሪክ ባለቤት መሆኗን አንስተው፥ ኪን ኢትዮጵያ ጉዞ የኢትዮጵያን ፀጋ ለአለም ለማስተዋወቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በቻይና ለሶስት ቀናት በነበረው የኪን ኢትዮጵያ ጉዞ በቻይናና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ ትስስር ለመደገፍ አይነተኛ ሚና ተወጥቷል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፥ቀጣይነት ያለው የህዝብ ለህዝብ ትስስርና የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት መፈረሙን ገልፀዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው፥ ሁለተኛው የኪን ኢትዮጵያ ጉዞ ከጳጉሜን 4 ቀን 2017 ጀምሮ እስከ መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ሩሲያ ለዘመናት የዘለቀ ዲፕሎማሲ፣ የባህልና ጥበብ ግንኙነት መመስረታቸውን ጠቅሰው፥ ጉዞው የኢትዮጵያና ሩሲያን የባህል ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
በሴንት ፒተርስበርግና ሞስኮ በሚካሄደው የጥበብ ትዕይንት የተለያዩ ኹነቶች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
የሻኩራ ፕሮዳክሽን ባለቤትና ማናጀር ካሙዙ ካሳ በበኩሉ፥ በሩሲያ በሚኖራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ባህል የሚያሳዩና ሌሎች ትዕይንቶች እንደሚቀርቡ ተናግሯል።