ዲስትሪክቶቹ ለዘመን መለወጫ በዓል መዋያ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ዲስትሪክቶቹ ለዘመን መለወጫ በዓል መዋያ ድጋፍ አደረጉ
ደሴ/ደብረ ማርቆስ ፤ ነሐሴ 30/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደሴና ደብረማርቆስ ዲስትሪክቶች የአዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች የገንዘብ፣ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አበረከቱ።
በባንኩ የደሴ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሰኢድ ዓሊ እንደገለጹት፣ የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል አስመልክቶ በደሴ ከተማ ለሚገኙ 200 አቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደርጓል።
ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለእያንዳንዳቸው 25 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ አምስት ሊትር ዘይትና ለዶሮ መግዣ አንድ ሺህ 300 ጥሬ ብር ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ባንኩ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ በመሰረተ ልማትና በሌሎችም ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ተሳትፎ በማድረግ በማህበራዊ ተሳትፎ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተወካይ ወይዘሮ ትዝታ ወንድሙ በበኩላቸው አስተዳደሩ እንደኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሉ አጋር አካላት ጋር በመተባበር የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ እየሰራ ነው ብለዋል።
የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አቶ መሐመድ ሀሰን በሰጡት አስተያየት አቅመ ደካማ በመሆናቸው የተደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን ተደስተው እንዲውሉ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላዋ የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ በለጡ ሰኢድም በተደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን በደስታ ለመዋል የሚያስችላቸው በመሆኑ ምስጋና አቅርበዋል።
በተያያዘ ዜና በባንኩ የደብረማርቆስ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ አፈወርቅ ሰንደቁ እንደገለጹት 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ ለ228 አቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደርጓል።
ድጋፉ የተደረገውም የመውሊድና የመጪውን አዲስ ዓመት በአል ምክንያት በማድረግ መሆኑን ጠቁመው ድጋፉም የስንዴ ዱቄት፣ አምስት ሊትር ዘይትና ጥሬ ገንዘብ መሆኑን አስረድተዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ተወካይ ወይዘሮ ትግስት ልየው እንዳሉት ባንኩ ችግረኞችን በመለየት ያደረገው ድጋፍ የሚመሰገንና ሊበረታታ የሚገባው ነው።
በድጋፉ ርክክብ ላይ የተገኙት ርዕሰ ርዕሳን አባ ሃይለማሪያም ታገለ እንዳሉት" መስጠት መታደል ነው" ባንኩ እግዚአብሔር የሚያዘውን በማድረጉ አርአያ ያደርገዋል ብለዋል።
የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ሰብሳቢ ሺኸ ኡመር ኢብራሄም በበኩላቸው "ነብያችን እርሱ ጠግቦ እየበላና እየጠጣ ጎሮቤቱ ሲራብ ዝም ያለ ከእኛ አይደለም ይላል" ብለዋል።
ባንኩ መተጋገዝን መተሳሰብን ታላሚ የማድረግ ስራ ማከናወኑንና በድርጊቱ መደሰታቸውንም ሰብሳቢው ተናግረዋል።