ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በታዳሽ ሀይል የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የተግባር እርምጃ ጀምራለች -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በታዳሽ ሀይል የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የተግባር እርምጃ ጀምራለች -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በታዳሽ ሀይል ልማት ብዝሃ ህይወትን መጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የተግባር እርምጃ እየወሰደች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ስብሰባ ቅድመ ጉባኤ አካል የሆነው የአፍሪካ ወጣቶች የአየር ንብረት ስብሰባ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አፍሪካ በዓለም የበካይ ጋዝ ልቀት ከአራት በመቶ በታች ብቻ ድርሻ ቢኖራት የዓለም ስጋት የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ በተለይም ለአፍሪካ ኢኮኖሚ፣ የኑሮ ሁኔታና ለአፍሪካ መጻዒ ተስፋ ስጋት ነው።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራና በታዳሽ ሀይል አመርቂ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸዋል።
የታዳሽ ሀይል ማዕከል እየሆነች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ ለጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ኬንያ ኃይል እያቀረበች መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ስኬት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም መሰረት መሆኑን ጠቁመው፤ ወጣቶች፣ ማህበረሰቡና መንግስት በጋራ ሁሉንም ማሳካት እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል።
በ2011 ዓ.ም በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እስከ 2018 ዓ.ም 50 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እስካሁን ወደ 48 ቢሊዮን የሚጠጋ በማሳካት በዓለም ትልቅ የደን መልሶ ልማት ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
አፍሪካ ስጋት ብቻ ሳይሆን ተስፋ ያላት አህጉር መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዕድሚያቸው ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ከ60 በመቶ በላይ ወጣቶች ያሉባት አህጉር መሆኗንም ጠቅሰዋል።
እነዚህ ወጣቶች ፈተናዎችን የሚወርሱ ብቻ ሳይሆን በኢኖቬሽን እና ፈጠራ መፍትሔ የሚያመነጩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው የመጀመሪያው የወጣቶች የአየር ንብረት ስብሰባ "የናይሮቢ የወጣቶች መግለጫ" ውሳኔ ሰጭዎች እይታቸውን እንዲቀይሩ በማድረግ ታሪክ መሰራቱን ገልጸው፤ የዘንድሮው የ"አዲስ አበባ የአየር ንብረት እና ልማት ቃል ኪዳን" መጋቢ መሆን አለበት ብለዋል።
ወጣቶች ፖሊሲ ግብዓት አመንጪዎች፣ ፈጣሪዎች፣ ውሳኔ ሰጭዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወጣቶች ከተነሳሽነት ባለፈ ዘላቂ ትብብር፣ ሀብት፣ ጥምረት እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ አጋር አካላት፣ መንግስታት ለወጣቶች ልማት፣ ሥራ ፈጠራ፣ መሪነትና አቅማቸውን ለማሳደግ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ያለወጣቶች ተሳትፎ ሊሳካ አይችልም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ከተናጠል ይልቅ በጋራ መቆም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ወጣቶች ለአፍሪካ የሚበጅ በትልቁ ማለም፣ ድምፃቸውን ከፍ አድርጎ ማሰማት፣ በአፍሪካ ያለውን ዕምቅ አቅም መጠቀም የሚያስችል ፈጠራና ኢኖቬሽን ላይ ማተኮር እና ድንበር ተሻጋሪ ትብብር መፍጠር አለባቸው ብለዋል።