ቀጥታ፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአፍሪካ አዲስ ንጋትና አዲስ ዘመን እንደመጣ የሚያሳይ ፕሮጀክት ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካ አዲስ ንጋትና አዲስ ዘመን እንደመጣ የሚያሳይ ፕሮጀክት መሆኑን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት "በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት በማካሄድ ላይ ነው።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዛዲግ አብርሃ በመድረኩ ባቀረቡት የመወያያ ሀሳብ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ አንገቷን ደፍታ የነበረች ሀገር በራሷ አቅም መነሳቷን ያስመሰከረችበት ነው ብለዋል።

ግድቡ የድል ታሪክ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ላይ ሲሰነዘሩ የነበሩ የትናንት መጥፎ ትርክቶችን የቀየረ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ትልቁ ግድብ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካ አዲስ ንጋትና አዲስ ዘመን እንደመጣ የሚያሳይ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።


 

ግድቡ የድፍረትና የቁርጠኝነት ውጤት መሆኑን በማንሳት ከድህነት እና ጨለማ ጋር አንኖርም የሚለውን ድምጻችንን ከፍ አድርገን ያሰማንበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን ይጨርሳሉ የሚል አዲስ ትርክት የፈጠረና የኢትዮጵያ ማንሰራራት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ትውልድ አሻራውን ያኖረበት የኢትዮጵያ የልዕልና ማብሰሪያ እንደሆነም አስረድተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አይቻልም የተባለውን መገንባት የሚችል ትውልድ መፈጠሩን ያስመሰከረና የአፍሪካ የመፈጸም አቅም ለዓለም ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ በራስ አቅም በራስ ገንዘብ የተሰራ የአፍሪካ የህዳሴና የመነሳት ሐውልት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም