በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አማካኝነት የሚፈጠረውን የቱሪዝም ሀብት ለመጠቀም ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አማካኝነት የሚፈጠረውን የቱሪዝም ሀብት ለመጠቀም ዝግጅት ተደርጓል
አሶሳ፤ ነሐሴ 30/2017 (ኢዜአ)፦ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አማካኝነት የሚፈጠረውን የቱሪዝም ሀብት ለመጠቀም ዝግጅት መደረጉን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጥቂት ቀናት በኃላ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "በጉባ ላይ ወግ" በነበራቸው ቆይታ መናገራቸው ይታወቃል።
ግድቡ የሚገኝበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ ለህዳሴው ግድብ ጉብኝት የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ለማስተናገድና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ላይ ይገኛል።
ይህንን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ምስክያ አብደላ እንዳሉት ግድቡን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች ከግድቡ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ለማድረግ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ እየተሰሩም ነው።
ጎብኚዎች ወደ ግድቡ ሲሄዱ ሙዚየሞች፣ ፏፏቴዎችና ቤተ መንግሥታትን ጨምሮ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ላይ ሊጎበኙ የሚችሉ የቱሪዝም ቦታዎችን የማልማት ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ያሉት ኃላፊዋ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የጋራ ዕቅድ በማዘጋጀት የቱሪዝም ሀብቱን ይበልጥ ለማልማት እና ለመጠቀም እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ቢሮው አስጎብኚ ወጣቶችን በማሰልጠን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዝግጅት ማድረጉንም አብራርተዋል።
ግድቡ የክልሉን ኢኮኖሚ በተለያዩ ዘርፎች በመደገፍ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረውም ኃላፊዋ ተናግረዋል።