ቀጥታ ስርጭት

በአፋር ክልል ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ሊቋቋሙ ነው

ሰመራ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች  ሊቋቋሙ መሆኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋምና ዕውቅና ለመስጠት የሚያስችሉ መሠረታዊ መስፈርቶችን ለመደንገግ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።


 

በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አስኬር መሐመድ እንዳመለከቱት፤   የአፋር ህዝብ ለረጅም ዘመናት በባህላዊ ዳኝነት ስርዓት ሲገለገል ቆይቷል።

ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠል ሕብረተሰቡ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተጨማሪ በአቅራቢያው የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ዳኝነት እንዲያገኝ ማድረጉ ለፍትህ ስርዓቱ መጠናከርና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በቶሎ እንዲፈቱ የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል። 

በክልሉ ፍትህ ቢሮ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር አቶ አህመድ ገአሰ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ አራት መድረኮችን በማዘጋጀት ውይይት ተደርጓል።


 

ይህም ውይይቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መሆኑን  ጠቅሰው፤ በዚህም በግብአትነት የሚውሉ መረጃዎች ማሰባሰብ መቻሉን አንስተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት የቢዱ ወረዳ ፍትህ ጽሕህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሐው ሻሚ፤ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትን ዕውቅና ለመሥጠት የተደረገው ውይይት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።


 

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች መቋቋማቸው የሕብረተሰቡን ጊዜና ገንዘብ ከመቆጠብ ባሻገር መደበኛ ፍርድ ቤቶችን በማገዙም ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው  የውይይት መድረክ ከክልሉ ከዞኖችና ወረዳዎች የፍትህ ጽህፈት ቤት የተወጣጡ አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም