ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከተሞችን በማዘመን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው-አሕመዲን መሐመድ(ዶ/ር) 

ባሕርዳር፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ከተሞችን በቴክኖሎጂ በማዘመን  ለነዋሪዎች፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም የተመቹ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ዘርፍ አስተባባሪ  እና የክልሉ  ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ  በባሕርዳር  ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ዘርፍ አስተባባሪና  የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ከተሞች ያላቸውን ፀጋ ሳይንሳዊ ዕውቀትን በመጠቀም ማልማትና ማሳደግ ያስፈልጋል።

ለዚሕም የውስጥ የገቢ አቅምን በማሳደግ ሕዝብ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች ዘላቂነት ባለው መንገድ እልባት መስጠት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

የከተሞች መስፋፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይሕንን በመሰረተ ልማት ከገጠሩ ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከተሞች ለነዋሪዎች፣ ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ  ለሌሎች ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች  የተመቹ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የአገልግሎት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማሳደግም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የተጀመሩ ስራዎች ልምዶችን በማካተት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ የሀገር ውስጥና የውጭ ከተሞችን ቴክኖሎጂ ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናን ይበልጥ  ለማሳደግ  መልካም ተሞክሮን ለመለዋወጥ እንደሚያግዝም  ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር  አንዱዓለም ጤናው፤ የትብብር መድረኩ 113 ከተሞችን በአባልነት በማቀፍ ልምድና ተሞክሮ ልውውጥ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።


 

በዚሕም የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት  የተመጣጠነ  እድገት እንዲኖር  የሚያስችሉ ተግባራት ላይ መሰረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በከተሞች ልማትን በማስፋፋት ለኑሮ የተመቹ እንዲሆኑ እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ለዚሕም የከተማ አስተዳደር መሪዎች እርስ በእርሳቸውና ከውጭ  ከተሞች የልምድ ልውውጥ እየተደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ከተሞች በመሰረተ ልማትና በቴክኖሎጂ ታግዘው የአሰራር ቅልጥፍናቸውን ይበልጥ  ለማሳደግ  ትኩረት መሰጠቱን አብራርተዋል።

የባሕር ዳር ከተማን የተፈጥሮ ፀጋ አጉልቶ በማውጣት ለነዋሪዎች፣ ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት የተመቸ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው ያሉት ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ናቸው።


 

የከተማውን የውስጥ ገቢ በማሳደግም የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጥያቄ መመለስ የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ስራዎች እየተስፋፉ መሆኑን አመልክተው፤ በትብብር መድረኩ መሳተፋችን  ልምድ የምንቀስምበት ይሆናል ብለዋል።

መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ፤ የክልልና የከተማ አስተዳደር አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም