ወጣቶች የአህጉሪቷን ጸጋዎች በዕውቀትና በክህሎት በመጠቀም ዘላቂ ትብብር መፍጠር ይገባቸዋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች የአህጉሪቷን ጸጋዎች በዕውቀትና በክህሎት በመጠቀም ዘላቂ ትብብር መፍጠር ይገባቸዋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡-በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ወጣቶች የአህጉሪቷን ጸጋዎች በዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም ዘላቂ ትብብር መፍጠር እንደሚገባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ስብሰባ ቅድመ ጉባኤ አካል የሆነው የአፍሪካ ወጣቶች የአየር ንብረት ስብሰባ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።
በመርሀ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የፓን አፍሪካ የአየር የአየር ንብረት ለውጥ ፍትህ ጥምረት ዋና ዳይሬክተር ሚቲካ ምወንዳ እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ወጣቶች ታድመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አፍሪካ በዓለም የበካይ ጋዝ ልቀት ከአራት በመቶ በታች ብቻ ድርሻ ቢኖራትም የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ስጋት ቢሆንም በተለይ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ፣ የኑሮ ሁኔታና ለአፍሪካ መጻዒ ተስፋ ስጋት ነው።
አፍሪካ ስጋት ብቻ ሳይሆን ተስፋ ያላት አህጉር መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ከ60 በመቶ በላይ ወጣቶች ያሉባት አህጉር መሆኗንም ጠቅሰዋል።
እነዚህ ወጣቶች ፈተናዎችን የሚወርሱ ብቻ ሳይሆን በኢኖቬሽን እና ፈጠራ መፍትሔ የሚያመነጩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው የመጀመሪያው የወጣቶች የአየር ንብረት ስብሰባ "የናይሮቢ የወጣቶች መግለጫ" የውሳኔ ሰጭ እይታቸውን እንዲቀይሩ በማድረግ ታሪክ መሰራቱን ገልጸው፤ የዘንድሮው የ"አዲስ አበባ የአየር ንብረት እና ልማት ቃል ኪዳን" መጋቢ መሆን አለበት ብለዋል።
ወጣቶች ፖሊሲ ግብዓት አመንጪዎች፣ ፈጣሪዎች፣ ውሳኔ ሰጭዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወጣቶች ከተነሳሽነት ባለፈ ዘላቂ ትብብር፣ ሀብትና ጥምረት እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ አጋር አካላት፣ መንግስታት ለወጣቶች ልማት፣ ሥራ ፈጠራ፣ መሪነትና አቅማቸውን ለማሳደግ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራና በታዳሽ ሀይል አመርቂ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እስከ 2018 ዓ.ም 50 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እስካሁን 48 ቢሊዮን በማሳካት በዓለም ትልቅ የደን መልሶ ልማት ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የታዳሽ ሀይል ማዕከል እየሆነች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ ለጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ኬንያ ኃይል እያቀረበች መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ስኬት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም መሰረት መሆኑን ጠቁመው፤ ወጣቶች፣ ማህበረሰቡና መንግስት በጋራ ሁሉንም ማሳካት እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ያለወጣቶች ተሳትፎ ሊሳካ አይችልም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ከተናጠል ይልቅ በጋራ መቆም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ወጣቶች ለአፍሪካ የሚበጅ በትልቁ ማለም፣ ድምፃቸውን ከፍ አድርጎ ማሰማት፣ በአፍሪካ ያለውን ዕምቅ አቅም መጠቀም የሚያስችል ፈጠራና ኢኖቬሽን ላይ ማተኮር እና ድንበር ተሻጋሪ ትብብር መፍጠር አለባቸው ብለዋል።