ቀጥታ፡

ለሀገር የማንሰራራት ጉዞ በመደመር እሳቤ የጋራ ትጋትና ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል- ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ) ፡- ለሀገር የማንሰራራት ጉዞ በመደመር እሳቤ የጋራ ትጋትና ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

በክልሉ የተከናወኑ እና በሂደት ላይ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ተግባራትና  የተገኙ ስኬቶችን በተመለከተ ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ  ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ፤  በለውጡ ዓመታት በክልሉ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን  አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ስኬት እውን የሚሆነው የሁሉም የተቀናጀ  ጥረት ሲታከልበት መሆኑን ገልጸው፤  በዚህ ረገድ በክልሉ በሁሉም ዘርፎች  ውጤታማ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ለሀገር የማንሰራራት ጉዞ በመደመር እሳቤ የጋራ ትጋትና ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በክልሉ የቱሪዝም ልማት፣ ኢንቨስትመንት፣ የግብርና በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የሰብል እና የአረንጓዴ ልማት በስፋት በማከናወን ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። 

በገጠርም ይሁን በከተሞች የህዝብን  ጥያቄዎች መሰረት ያደረጉ የልማት ተግባራትን  የማስፋፋትና ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎች ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን አብራርተዋል።

በክልሉ በተለይም የቡና ምርትና ምርታማነት ከፍተኛ እድገትና ማንሰራራት ማሳየቱን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መልካም እድሎችን በመጠቀም በሌሎችም የግብርና ዘርፎች በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በቀጣይም ሰላምን በማጽናትና የጋራ ትርክትን በመገንባት ለልማት አጀንዳዎች ትኩረት በመስጠት  የበለጸገችና ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ጥረታችን ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም