ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እና በህብረት ያሳኩት ድል ነው - አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እና በህብረት ያሳኩት ድል ነው - አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እና በህብረት ያሳኩት ድል መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት "በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት በማካሄድ ላይ ነው።
በመድረኩ የተለያዩ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በማሳካት በህብረት ያለምንም ድምጽ ዓድዋን ደግመነዋል በማለት በታታሪ ትውልድ ግድቡ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ ባለፉት 14 አመታት በርካታ ተግዳሮቶችን ማለፉን ገልጸው ይህንንም በህዝብ እና በመንግስት አቅም ተረባርበን ተሻግረነዋል ብለዋል።
ጽህፈት ቤቱም ህብረተሰቡን በአንድነት በማሰለፍና ሁለንተናዊ ድጋፍ በማስተባበር ሚናውን መወጣት መቻሉን ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስኬት ለሌሎች ድሎች መረማመጃ እንደሚሆን ጠቁመው፤ ግድቡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እና በህብረት ያሳኩት ትልቅ ድል መሆኑን ገልጸዋል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ሞቱማ መቃሳ በበኩላቸው፤ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሳኩት የትውልዱ ድል ነው ብለዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያውያን ቁጭታቸውን ወደ ተግባር የቀየሩበት ስኬታማ ስራ መሆኑን ጠቁመው፤ በህብረት መነሳት ከተቻለ ማሳካት የማይቻል ነገር እንደሌለ የህዳሴ ግድብ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በህብረት ለልማት መሰለፍ ውጤታማ እንደሚያደርግ ከህዳሴ ግድብ ስኬት ተምረንበታል ብለዋል።