ሥራን በብቃትና በጥራት መከወን ጊዜው የሚጠይቀው አርበኝነት ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
ሥራን በብቃትና በጥራት መከወን ጊዜው የሚጠይቀው አርበኝነት ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፦ሥራን በብቃትና በጥራት መከወን ጊዜው የሚጠይቀው አርበኝነት ነው ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ISO 9001-2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የተጠሪ ተቋማት አመራር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001) ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መለኪያ መስፈርት ሲሆን፤ ምርቶች ወይም አገልግሎቶች የጥራት ደረጃቸው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደርጋል።
በሌላ በኩል ሥራና አገልግሎቱ ወይም ምርቱ ደንበኛን በሚያረካ መልኩ የአሠራር ሥርዓትን ተከትሎ እንዲከወን የሚያስችል ሂደት ነው።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ISO 9001-2015 የጥራት ሥራ አመራር ትግበራ በመፈጸም ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቷል።
በተዘጋጀው የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ የዘርፉን ተልዕኮ ማሳካት የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች ሲተገብር ቆይቷል።
የለውጡን መሳሪያዎች አሰናስኖ በመጠቀም ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ጠቁመው፤ በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የተቀመጡ መስፈርቶችን ለማሟላት በትጋት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ዓለም አቀፍ ዕውቅናውም ተቋሙን ለበለጠ ትጋት የሚያነሳሳ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ተቋማት ጥራትን የመለያ መንገዳቸው በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሁላችንም በትጋት መስራት አለብን ብለዋል።
ሥራን በብቃትና በጥራት መከወን ጊዜው የሚጠይቀው አርበኝነት መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
አሁን የተገኘው ዕውቅና የቴክኒክና ሙያ ሥራን ጨምሮ ተቋማቸው የሚያከናውናቸውን ተግባራት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።
በቀጣይም በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የተቀመጡ መስፈርቶችን በማሟላትና ወጥነት ያለው አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር ሁሉም እንዲተጋ ጠይቀዋል።