ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ45 ሺህ በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና አጠናቀው የምስክር ወረቀት ወስደዋል

ወላይታ ሶዶ ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  ከ45 ሺህ በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና አጠናቀው የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን የክልሉ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የቢሮው ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጋሎ በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን በማጠናከር ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከተጀመረ ወዲህ ከ100 ሺህ 700 በላይ ዜጎች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

‎ከተመዘገቡት ውስጥ ከ37 ሺህ 537 በላይ የሚሆኑት በአራቱም የቴክኖሎጂ ዘርፎች ስልጠናውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

‎ከነዚህ መካከልም እስካሁን ከ45 ሺህ 95 በላይ የሚሆኑት ስልጠናውን አጠናቀው የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን አቶ ተካልኝ  ተናግረዋል።

ለአብነት በክረምቱ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በስልጠናው እንዲሳተፉና እንዲሁም ከ4 ሺህ 159 በላይ የመንግስት ሰራተኞችም መሰረታዊ የዲጂታል ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ጠቁመዋል።

‎በክልሉ በወላይታ ዞንም በርካታ ዜጎች ተመዝግበው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትን ለማስፋት መንግስት ባመቻቸው ዕድል ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ የዞኑ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ አሉላ ተናግረዋል።


 

በዞኑ ስልጠናው ከተጀመረ ወዲህ 20 ሺህ 266 ሰልጣኞች የተመዘገቡ ሲሆን 14 ሺህ 671ዱ ስልጠናውን አጠናቅቀው የምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸው አመልክተዋል።

ለሦስት ዓመታት በሚቆየው ስልጠናም ለ69 ሺህ 200 ሰዎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ፣ በአንድሮይድ ልማት እና በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ላይ አተኩሮ እየተሰጠ ያለው ስልጠና በዲጂታል ክህሎት የዳበረ ማህበረሰብ ከመፍጠር ባለፈ የዲጂታል ክህሎት ክፍተትን ለመሙላት ያግዛል ብለዋል።

በወላይታ ሶዶ ከተማ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ ተክሌ ባሳ ስልጠናው በዘርፉ የላቀ ዕውቀት እንዲያገኙና ያለ አግባብ ይባክን የነበረ ጊዜን በመልካም ሁኔታ እንዲያሳልፉ ማድረጉን አስረድተዋል።


 

ስልጠናው የኮምፒውተር ክህሎትን በማሳደግ ከጠባቂነት ተላቅቀን በራሳችን ስራ እንድንፈጥር አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል።

ስልጠናው ዲጂታል ቴክኖሎጂን በተመለከተ ተጨማሪ ዕውቀት ሰጥቶኛል የሚሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ማቴዎስ ዋዳ መጪውን ዓለም የሚመጥን ዕውቀት መቅሰማቸውን ተናግረዋል።


 

በስልጠናው 3 የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ጠቁመው የለውጡን ፍጥነት በመቀላቀል ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች ለማጋራት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም