ቀጥታ፡

የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በወንዞቿ መጠቀም የሚችል አቅም እንደፈጠረች ማሳያ ነው - ምሁራን

ወላይታ ሶዶ ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በወንዞቿ መጠቀም የሚችል አቅም እንደፈጠረች ማሳያ መሆኑን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጉቼ ጉሌ(ዶ/ር) የኢትዮጵያዊያን የጥንካሬ መገለጫና የህብረታቸው ማሳያ የሆነው ግድቡ መጠናቀቁ ሐሴት እንደፈጠረባቸው ጠቅሰዋል፡፡

የግድቡ መጠናቀቅ በዜጎች ዘንድም የይቻላል መንፈስን የፈጠረና አዲስ ታሪክ የተጻፈበት  ድል መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ በጠንካራ የፕሮጀክት አመራር በርካታ ፈተናዎችን ተሻግሮ መጠናቀቁ በህዝቡ ዘንድ የፈጠረውን መነሳሳት ሌላ አዲስ ፕሮጀክት ለመጀመር መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ደነቀ ዳና(ዶ/ር) በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያንን አገራዊ ፍቅርና አንድነት የመለሰ የአገር ካስማ ነው ብለዋል ።


 

ግድቡ ለዘመናት ለባዕዳን ይፈስ የነበረው ውሃ ለአገሩ ግልጋሎት እንዲሰጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ከመሆኑም በላይ የአገሪቱን የውሃ ሀብት አጠቃቀም የቀየረ ነው ብለዋል።

የግድቡ ተጀምሮ መጠናቀቅ አንደኛው ምዕራፍ ነው ያሉት ደነቀ (ዶ/ር) በሂደቱ መንግስት የወሰደው ቁርጠኝነት የኢትዮጵያን አይበገሬነትን ለዓለም ዳግም ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ቋንቋ ማናገሩን ጠቁመው ለነገ ተስፋ የሚሰንቁ ሌሎች ፕሮጀክቶች መጀመር እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።

የአይቻልምን መንፈስ የቀለበሰው የህዳሴ ግድብ አዲስ ታሪክ የተጻፈበት ድል በመሆኑ የተፈጠረውን መነቃቃት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመድገም ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ትግል ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም