የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ዝግጅት ተደርጓል-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ዝግጅት ተደርጓል-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመጪው የዘመን መለወጫ ዕለትና በዋዜማው የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ዝግጅት ማድረጉን ገለፀ።
የአገልግሎቱ የኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር በበዓሉ ወቅት ሊከሰት የሚችል የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የተደረጉ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም በአዲስ አበባ ከ15 በላይ የዞን ኦፕሬሽን ቡድን ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀው፤ በክልሎችም በተመሳሳይ መልኩ የተመሰረተ ግብረ ሀይል ወደ ስራ መግባቱን ነው ያመለከቱት፡፡
አገልግሎቱ በሀገር አቀፍ ደረጀ የኃይል ጫና እና የመስመር እርጅና አለባቸው ተብለው የታሰቡ 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ኃይል ተሸካሚ መስመሮችን በመፈተሽ ማስተካከያ መድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ37 ሺህ 699 ኃይል ተሸካሚ ትራንስፎርመሮችን በመፈተሽ ማስተካከያ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
አገልግሎቱ በዋዜማውና በዘመን መለወጫ ዕለት ሊያጋጥም የሚችለውን የሀይል መቆራረጥ እና መዋዥቅ ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በበዓሉ ወቅት የኃይል መቆራረጥ ቢከሰት አስቸኳይ የጥገና ስራ ለማከናወን 24 ሰዓት ምላሽ የሚሰጥ ግብረ ሀይል መዋቀሩን አስታውቀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛበት በተለይም ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ባሉት ጊዜያት ኤሌክትሪክ መጠቀም የተሻለ አማራጭ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ደንበኞችም በበዓሉ ወቅት ሊደርስ የሚችለውን አላስፈላጊ ወረፋ ለመቀነስ ቀድመው ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡