በክልሉ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚስተዋልን ህገወጥ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪን ለመከላከል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚስተዋልን ህገወጥ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪን ለመከላከል ዝግጅት ተደርጓል
ሚዛን አማን፤ ነሐሴ 30/2017 (ኢዜአ):- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መጪውን የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ አግባብነት የሌለው የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ተገነ አንጎ ለኢዜአ እንዳሉት በዓላትን ተከትሎ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የተሳፋሪ ፍሰት ይጨምራል።
በዚህም ሳቢያ የሚፈጠረውን የተሽከርካሪ እጥረት ምክንያት በማድረግ አላግባብ ታሪፍ በመጨመር ኅብረተሰቡን ለጫና የሚዳርጉ አሽከርካሪዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ይህን ህገወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አሽከርካሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በቅንጅት ለመውሰድ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።
በበዓሉ ወቅት የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥር የማድረግ ሥራን ከመደበኛ ትራፊክ ፖሊሶች ባሻገር ሁሉም የፖሊስ አባላት በየአካባቢው ቁጥጥር እንዲያደርጉ የጋራ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል።
በሌላ በኩልም የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት አሽከርካሪዎች የጥንቃቄ መመሪያዎችን ጠብቀው ማሽከርከር እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
በቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ላይ ትራፊክ ፍሰት ቁጥጥርና ክትትል ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አድነው አሰፋ በትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ይጠናከራል ብለዋል።
የትራፊክ ደንቡ ላይ የተቀመጠውን የቅጣት መጠን በግብረ ኃይል በማሻሻል አስተማሪ ቅጣት የመውሰድ ሥራ መጀመሩን አመልክተዋል።
በተለይ ከዞኑ ሚዛን አማን ከተማ፣ ቦንጋ፣ ዲማ፣ መገንጠያና እና ቴፒ ከተሞች ያለውን የተሳፋሪ ፍሰት መብዛት መነሻ በማድረግ በደላሎች የሚደረገውን የታሪፍ ጭማሪ ለመከላከል በልዩነት የመከታተሉ ተግባር ይጠናከራል ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች መካከል የቤንች ሸኮ ዞን ነዋሪ አቶ ዮሐንስ አቱሞ ኅብረተሰቡ በታሪፍ ጭማሪ ምክንያት የኢኮኖሚ ጫና እንዳይፈጠርበት ቁጥጥሩ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የትራፊክ ፖሊሶች በየመንገዱ እያስቆሙ ቁጥጥር የሚያደርጉ ከሆነ መረጃ በመስጠት የትራንስፖርት ሕግ ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን አክለዋል።
በዓላትን እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር ያልተገባ ጥቅም ከማግኘት እሳቤ በመውጣት መተሳሰብን ማስቀደም አለብን ያሉት ደግሞ አቶ ሲዩም ካሳ የተባሉ የካፋ ዞን ነዋሪ ናቸው።
የተሽካርካሪ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የስምሪት ሂደቱን በማሻሻል መንግሥት ዜጎችን ከእንግልት የመታደግ ተግባሩን ሊያጠናክር እንደሚገባም አክለዋል።