ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የጽናትና የአንድነት ድል ነው -የኪነጥበብ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የጽናትና የአንድነት ድል ነው -የኪነጥበብ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የፅናት፣ የትዕግስትና የአንድነት ድል መሆኑን የተለያዩ ክልሎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ገለፁ።
በሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድር እየተሳተፉ የሚገኙ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የህዳሴ ግድብ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ፕሮጀክት በመሆኑ ተጠናቆ ማየታቸው ትልቅ ደስታ ፈጥሮላቸዋል።
ከሐረሪ ክልል የመጣው አብዱራህማን አብራር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ህብረት፣ ጥንካሬ እና አልበገር ባይነት እንዲሁም በጋራ መቆም ያስገኘው ድል መሆኑን ተናግሯል።
ግድቡ ለፍጻሜ በቅቶ መመልከትና የዚህ አኩሪ ታሪክ አካል መሆን ትልቅ ዕድል ነው ብሏል።
ከአማራ ክልል የመጣው አየነው አስራት በበኩሉ፥ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን ያኖሩበት የህዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ መደሰቱን ገልጿል ።
ግድቡ ኢትዮጵያውያንን ወደ ብርሃንና ወደ ከፍታ የሚያሸጋገር መሆኑንም ጠቁሟል።
ከሲዳማ ክልል የመጣችው ኦልብራይት ወልደመስቀል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያቆሙት የብሄር ብሄረሰቦች ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፃለች።
የግድቡ መጠናቀቅ ትውልዱ በይቻላል መንፈስ ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እንዲያሳካ ይበልጥ መነሳሳትን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።