የኢትዮጵያን ማንሰራራት በጥበብ ሥራዎቻችን የማብሰር ሚናችንን እንወጣለን-የኪነ-ጥበብ ውድድር ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ማንሰራራት በጥበብ ሥራዎቻችን የማብሰር ሚናችንን እንወጣለን-የኪነ-ጥበብ ውድድር ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን ልማትና ማንሰራራት በጥበብ ሥራዎች በማጉላት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድር ተሳታፊዎች ገለፁ።
ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድር "ጥበባት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ውድድሩ ከነሐሴ 28 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2017 የሚቆይ ሲሆን ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ ትናንት የመነባንብ፣ ሙዚቃና ውዝዋዜ እንዲሁም የፋሽን ትርኢት ውድድር አካሂደዋል።
ከተወዳዳሪዎቹ መካከል ከድሬዳዋ የመጣው ዮሐንስ ይርሳው፥ ጥበብ ሀገርን ለማልማት የሚያስችል ኃይል ያለው እንዲሁም ህብረትና አንድነትን የሚያጎለብት መሳሪያ ነው ብሏል።
ውድድሩ የአካባቢያቸውን ባህል ለማስተዋወቅ፣ የሌሎችን ባህል ለማወቅና ልምድ ለመቅሰም የሚያስችል መሆኑንም ተናግሯል።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጣችው ዮርዳኖስ አንተነህ በበኩሏ ውድድሩ የክልላችንን ባህል ለማስተዋወቅ የሚያስችል መድረክ ነው ብላለች።
የሀገር ልማትና ዕድገትን ለማረጋገጥ በኪነጥበብ ሥራዎቿ የበኩሏን ሚና እንደምትወጣ ገልጻለች።
ከሲዳማ ክልል የመጣችው ሜላት አብርሃም በበኩሏ ውድድሩ የጥበብ ተሰጥኦ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን የሚያበረታታ ነው ብላለች።
ጥበብ ለሀገር አንድነት ትልቅ ሚና እንዳላት የጠቀሰችው ሜላት ውድድሩ የሀገራችንን ታሪክ እንድናውቅና ያለንን አቅም ተጠቅመን ሀገራችንን እንድናስተዋውቅ አስችሎናል ስትል ተናግራለች።
የኢትዮጵያን ልማትና ማንሰራራት ለማብሰር የጥበብ ሚና የጎላ ነው ያለው ደግሞ ከሶማሌ ክልል የመጣው መሀመድ ካሊድ ነው።
ልማትን ለማረጋገጥ የህዝብ የተባበረ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።