የአፍሪካ እግር ኳስ ቆርቋሪዎቹ ኢትዮጵያ እና ግብጽ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ እግር ኳስ ቆርቋሪዎቹ ኢትዮጵያ እና ግብጽ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከግብጽ ጋር ዛሬ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በካይሮ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ይካሄዳል። 23ኛው የፊፋ እ.አ.አ በ2026 በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ የጣምራ አዘጋጅነት ይደረጋል።
ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከግብጽ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሴራሊዮን፣ ጊኒ ቢሳው እና ጅቡቲ ተደልድላ እስከ አሁን ስድስት ጨዋታዎችን አካሂዳለች።
ብሄራዊ ቡድኑ ዛሬ የምድብ ሰባተኛ ጨዋታውን ከግብጽ ጋር ያከናውናል። ዋልያዎቹ በስድስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ተጋጣሚዋ ግብጽ በ16 ነጥብ ምድቡን እየመራች ነው።አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከግብጽ እና ሴራሊዮን ጋር ለሚደረጉ ጨዋታዎች ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ቡድኑ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
አሰልጣኙ ሶስት ተጫዋቾችን ቀንሰው 23 ተጫዋቾች ማክሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ካይሮ አቅንተዋል።
ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ማምሻውን በካይሮ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በአሰልጣኝ ሆሳም ሀሰን የምትመራው ግብጽ ከኢትዮጵያ እና ሴራሊዮን ላለባት የማጣሪያ ጨዋታዎች ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅቷን ስታደርግ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ እና ግብጽ በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያላቸው ሀገራት ናቸው።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እ.አ.አ በ1957 በሱዳን ካርቱም ሲቋቋም መስራች ከነበሩ አራት አባል ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።
ሀገራቱ ለሰባት አስርት ዓመታት ገደማ የቆየ ፉክክር አላቸው። ካፍ በተቋቋመበት 1957 ግብጽ ባስተናገደችው የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ሁለቱ ሀገራት በፍጻሜው ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር 4 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1962 ባዘጋጀችው ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር ግብጽን 4 ለ 2 በማሸነፍ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ እና ብቸኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አግኝታለች።
በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2024 በተካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ እ.አ.አ በ2022 ባደረጉት የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ግብጽን 2 ለ 0 ማሸነፏ አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ እና ግብጽ በውድድርና የወዳጅነት ጨዋታዎች እስከ አሁን 19 ጊዜ ተገናኝተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ 3 ጊዜ ስታሸንፍ ግብጽ 14 ጊዜ ድል ቀንቷታል። 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በ19ኙ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ 16 ግቦችን ስታስቆጥር ግብጽ 57 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
ሀገራቱ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በመጋቢት ወር 2017 ዓ.ም ሞሮኮ ላይ አድርገውት በነበረው ጨዋታ ግብጽ 2 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ላይ ለመቆየት ከዛሬው ጨዋታ ሶስት ነጥብ ማግኘት ይጠበቅባታል።
የ33 ዓመቱ ደቡብ አፍሪካዊ አቦንጂል ቶም ጨዋታዋውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
ዋልያዎቹ በማጣሪያው ስምንተኛ ጨዋታቸውን ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም ከሴራሊዮን ጋር ያደርጋሉ።