ቀጥታ፡

ሰላምን ማጽናት የጸጥታ ተቋማት ዋነኛ ተልዕኳቸው ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፡-ሰላምን ማጽናት የጸጥታ ተቋማት ዋነኛ ተልዕኳቸው ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት የኢፌዴሪ የጸጥታ ተቋማት ዋነኛው ተልዕኮ ሰላምን በመላ ሀገሪቱ ማጽናት ነው ብለዋል፡፡ 

ይሄን በተመለከተ ከጸጥታ ተቋማት አመራሮች ጋር ሲደረግ የነበረው ውይይት ዛሬ መጠቃለሉን አመልክተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲሳካ ሰላምና ጸጥታ አስቻይ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ዋነኛው ግብዐትም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ይሄን ለማስከበር ሕዝባችን በባህሉና በዕሴቱ ላይ ተመሥርቶ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ፣ የጸጥታ ተቋማት ሚና የማይተካ ነው ብለዋል፡፡ 

የአሻጥር፣ የከተማና የገጠር ውንብድና፣ የኮንትሮባንድ፣ የሙስና፣ ሕገ ወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር እና የመሳሰሉ ወንጀሎችን በመከላከልና በመቆጣጠር የሕዝቡን ሰላም ማስከበር እንደሚገባ በውይይቱ ላይ በስፋት መነሳቱን ጠቁመዋል፡፡ 


 

የሰዎችና የሸቀጦች ዝውውር ለብልጽግናችን ወሳኝ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ስለዚህም በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ዝርፊያዎችን፣ እገታዎችን እና መሰናክሎችን በተጠና መንገድ መቆጣጠር ይገባናል ነው ያሉት፡፡ 

የጸጥታ ኃይላችን ሕዝቡን በየደረጃው በማስተባበር እነዚህን አካላት ከእኩይ ተግባራቸው መግታት፣ ብሎም ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባ አጽንዖት ተሰጥቶበታል ሲሉም አክለዋል፡፡ 

ታላላቅ መሠረተ ልማቶችን፣ የማዕድን ቦታዎችን፣ ኢንዱስትሪዎችን፣ የመኖሪያ አካባቢዎችን እና የሕዝብ መገልገያዎችን ደኅንነት ለመጠበቅና አገልግሎታቸው ያለ እንከን እንዲፈጽሙ ለማስቻል የጸጥታ አካላትና የየአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር ወሳኝ መሆኑን በውይይቱ ወቅት መነሳቱን አስታውቀዋል፡፡  

ሕዝቡ ሰላሙን በራሱ እጅ የማስከበር ፍላጎቱ፣ ዝግጁነቱና ዐቅሙ በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ተገምግሟል ነው ያሉት፡፡ 
ባህላዊና መንፈሳዊ ዕሴቶቹን በመጠቀም የታጠቁ አካላት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮ የአካባቢውን ሰላም እያስከበረ ነው ብለዋል፡፡ 

የጸጥታ አካላት ለሚያከናውኑት ሥምሪትም የመረጃና የሎጂስቲክስ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንን ጠቁመዋል፡፡ ይሄን የሕዝቡን ዐቅም ይበልጥ በሥልጠና በማጎልበት ለዘላቂ ሰላም መጠቀም እንደሚገባ በውይይቱ ማጠቃለያ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት፡፡  
  
የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ በማሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የሽብር ተግባር የሚፈጽሙትን ትኩረት ሰጥቶ መከታተል እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት የተነሣ ሲሆን፣ በሳይበር ቴክኖሎጂ በኩል መከናወን የሚገባቸው የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራዎች ይበልጥ መጠናከር እንደሚገባቸው በውይይቱ ተመልክቷል፡፡

በአንድ በኩል የቴክኖሎጂ የመከላከያና መቆጣጠሪያ ሥራዎችን ለመሥራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሽብር ፈጣሪዎቹን ለሕግ ለማቅረብ የጸጥታ አካላት በጽኑ መሥራት እንዳለባቸው መመሪያ ተሰጥቷል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡  

የጸጥታ ተቋማት ወትሮ ዝግጁነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር በሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱን በውይይቱ መገምገሙን ጠቁመዋል፡፡



ኢትዮጵያ ከዘመን ጋር የዘመኑ እና በሕገ መንግሥታዊ ዕሴቶች ላይ የተገነቡ የጸጥታ ተቋማት እየገነባች መሆኗ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ ይሄንን ግንባታ የዘወትር ተግባር በማድረግ መቼም፣ የትም፣ ለምንም ዓይነት ሁኔታ ዝግጁ የሆኑ የጸጥታ ተቋማትን እየገነባን እንድንሄድ የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካዊ ኩስመና ባከተመበትና ቁመናዋ እየተስተካለ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ የጸጥታ ተቋሞቻችን የሀገሪቱን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት፣ ዳር ድንበር፣ ሰላምና ደኅንነት፣ ብሎም የብልጽግና ጉዞ ለማስከበር በሚችሉበት ዐቅም እና ዐቋም ላይ እንደሚገኙ ተረጋግጧል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ይሄንኑ ወትሮ ዝግጁነት ይበልጥ በማጠናከር፣ የውስጥና የውጭ ችግር ፈጣሪዎችን አደብ አስገዝቶ፣ ሰላምን በሚያጸና ልክ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል የጸጥታ ተቋማት ዋና ተልዕኮ ሰላምን ማጽናት ነውና ሲሉም አስፍረዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም