ቀጥታ፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ህመሞች እስከ 30 በመቶውን የሚይዘው የጡት ካንሰር

በኢትዮጵያ ሴቶችን ከሚያጠቁ የካንሰር በሽታዎች ቀዳሚው የጡት ካንሰር መሆኑን በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የጡት እና እንዶክራይን ቀዶ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት፣ የቀዶ ሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የሕክምና ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ወንድወሰን አምታታው ተናግረዋል።

👉 የጡት ካንሰር ሁኔታ

• እንደ ዶክተር ወንድወሰን ገለጻ፤ የጡት ካንሰር ማለት በጡት ቲሹ ውስጥ የሚወጡ ከባድ እና በቁጥጥር ውስጥ ያልሆኑ ሕዋሶች መብዛት ነው።

• ይህ ካንሰር በአብዛኛው ሴቶችን የሚያጠቃ የካንሰር አይነት መሆኑን ገልጸዋል።

👉 ለጡት ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች

ምንም እንኳን ማንኛውም አይነት ካንሰር መነሻው በውል ባይታወቅም አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶች መኖራቸውን ዶክተር ወንድወሰን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከእነዚህም መካከል፡-

• የቤተሰብ ታሪክ (እንደ እናት፣ እህት ወይም ሴት ልጅ)፣ የዕድሜ መጨመር (ከ40 ዓመት በላይ መሆን)፣ ጡት አለማጥባት፣ የመጀመሪያ ልጅን ዘግይቶ መውለድ፣ የአካል ክብደት መጨመር፣ የስብ ክምችት መብዛት፣ የሆርሞን መጋለጥ (ለረጅም ጊዜ ለኤስትሮጅን መጋለጥ)፣ የአልኮል መጠጥ ማብዛት፣ ሲጋራ ማጨስ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ በዋናነት የሚጠቀሱ የጡት ካንሰር አጋላጮች መሆናቸውን አብራርተዋል።

👉 የጡት ካንሰር በአብዛኛው እነማንን ያጠቃል?

• የጡት ካንሰር ሁሉንም የዕድሜ ክልልና ጾታ እንደሚያጠቃ ገልጸው፤ በተለይም በአብዛኛው በዕድሜ ከ40 እስከ 60 ዓመት በላይ የሆኑትን ያጠቃል ብለዋል።

• የጡት ካንሰር በስፋት በሴቶች ላይ ቢከሰትም፤ አልፎ አልፎ በወንዶች ላይም እንደሚከሰት ጠቁመዋል።

👉 ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

• በጡት ላይ የሚከሰት እብጠት፣ ደም የቀላቀለ ፈሳሽ ከጡት መውጣት፣ የጡት ቆዳ ወደ ውስጥ መሰርጎድ፣ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መግባት፣ የጡት ቆዳ መልክ መቀየር እንዲሁም መሸብሸብ፣ የጡት መጠን እኩል አለመሆን፣ የንፍፊት እብጠት የመሳሰሉት ከጡት ካንሰር ምልክቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

👉 ለጡት ካንሰር ላለመጋለጥ ምን ማድረግ ይገባል?

• የጡት ካንሰርን ለመካላከል ቢያንስ የሚታወቁ የጡት ካንሰር አጋላጭ የሆኑት ላይ መሥራት እንደሚገባ መክረዋል ዶክተር ወንድወሰን።

ለአብነትም ጤናማ የሆነ እንቅስቃሴ እና ክብደትን ማስጠበቅ፣ ከፍተኛ የአልኮል መጠጥን መገደብ፣ ጡት ማጥባት ፣ ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች መደበኛ ጡት ምርመራ ማድረግ፣ የራስ የጡት ምርመራ ማድረግ እና ሌሎችንም ጠቁመዋል።

👉 ሕክምናውስ?

• የጡት ካንሰር ሕክምና ብዙ ባለሙያዎቸን የሚያሳትፍ መሆኑን አስታውቀው፤ የተለያዩ ሕክምናዎች እንዳሉት አስረድተዋል።

ከሕክምናዎቹ መካከልም፤ ቀዶ ጥገና፣ ራዲዮቴራፒ፣ ኬሞቴራፒ፣ የሆርሞን ሕክምናን ጨምሮ ሌሎችም በዋናነት እንደሚሰጡ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም