ቀጥታ፡

የሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የቅድመ ጉባኤ ውይይቶች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2017(ኢዜአ)፦ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ከዋናው ጉባኤ ቀደም ብሎ ለግዙፉ አህጉራዊ ሁነት መደላድል የሚፈጥሩ ቅድመ ጉባኤ ውይይቶች ከነሐሴ 30 እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳሉ።

በውይይቶቹ መንግስታት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የልማት አጋሮችና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ይሳተፋሉ። ይህም ሁሉን አሳታፊ ምክክር ለማድረግ ለተያዘው እቅድ እንደ መንደርደሪያ የሚያገለግል ነው።

አካባቢያዊ መፍትሄዎችን ከአህጉራዊ የአየር ንብረት ስትራቴጂዎች ጋር ማስተሳሰር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይደረጋል።

የመግቢያ ምክክሮቹ ማህበረሰብ ተኮር መፍትሄዎች ጎልተው የሚሰሙበት፣ የአፍሪካ የጋራ አጀንዳ የሚቀረጽበት እንዲሁም ሀገራት ለአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የማጣጣሚያ እቅድ እና ዘላቂ እድገት ሀገራት ጠንካራ ቃል ኪዳኖችን የሚገቡበት መሆኑን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።

የቅድመ-ጉባኤ ምክክሩ እስከ ጳጉሜን 1 /2017 ዓ.ም ከሚቆየው የአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት (CW2) ጋር የተሳሰረ ነው።

የካርቦን ገበያ፣ ጤና እና አየር ንብረት፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ማጠናከር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ አረንጓዴ ኢኖቬሽን፣ አረንጓዴ እድገት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲዎች ተጣጣሚነትና ቀጣናዊ ትብብር ውይይት ከሚደረግባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ዋና ጉባኤው በአየር ንብረት ፋይናንስ፣ ኢኖቬሽን፣ በማይበገር አቅም ግንባታ፣ በብሄራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅዶች ትግበራና ሌሎች የሚወያይባቸውን አጀንዳዎች የሚቀርጽ መሆኑን ህብረቱ ገልጿል።

በአጠቃላይ በቅድመ ጉባኤው ላይ የሚንሸራሸሩ ሀሳቦች ለሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡበት መሰረት የሚጥል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም