መንግሥት የኢ- ኮሜርስ ግብይትን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥቷል- ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የኢ- ኮሜርስ ግብይትን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥቷል- ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2017(ኢዜአ)፡-መንግሥት የኢ- ኮሜርስ ግብይት በሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ለማጠናከር በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ”ኢ-ኮሜርስ ለተሻለ ተወዳዳሪነት” በሚል መሪ ሀሳብ የኤሌክትሮኒክ ንግድ አገልግሎትን ለማዘመን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት መንግስት የንግድ ስርዓቱን ቀልጣፋና ተወዳዳሪ ለማድረግ በሰጠው ትኩረት የወጪ ንግድ ከፍተኛ ዕድገት እየተመዘገበበት ይገኛል።
በዓለም አቀፍ ገበያ ይበልጥ ተወዳዳሪ ለመሆን የንግድ እንቅስቃሴን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራን ለማፋጠን ባለድርሻ አካላት በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም ኢ-ኮሜርስን የሚያሳልጡ የቁጥጥርና የአሰራር ማዕቀፎች ተዘጋጅተው እንደሚተገበሩ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርዓያ ሥላሴ በበኩላቸው፥ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት በኤሌክትሮኒክ ግብይት መተማመንን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው አንስተዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) ኢ-ኮሜርስ ዲጂታል ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
ኢ-ኮሜርስን ለማስፋት ሰፊ የቴሌኮም መሰረተ ልማት መዘርጋቱንና የ4 ጂ እና 5 ጂ የኔትወርክ ማሻሻያ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት በኢትዮ-ቴሌኮም የሞባይል መኒ ዋና ኦፊሰር አቶ ብሩክ አድሃና ናቸው።
በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የናቹራል ላንጉዊጅ ፕሮሰሲንግ ዲቪዥን ኃላፊ ሮዛ ጸጋዬ (ዶ/ር)፥ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለ-ኢኮሜርስ መሳለጥ ጉልህ አበርክቶ ይጫወታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትም ለዘርፉ ቁልፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የራይድ መስራች እና ስራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ በበኩላቸው የዲጂታል አገልግሎት መስፋፋት በተሰማሩበት ዘርፍ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢ-ኮሜርስን እንደ ሀገር ለማስፋት የተጀመሩ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን በማንሳት፥ ከመሰረተ ልማት አንጻር ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡