የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ የተሻሻሉ አዳዲስ አሰራሮች ይተገበራሉ - ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ የተሻሻሉ አዳዲስ አሰራሮች ይተገበራሉ - ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዳማ፤ ነሐሴ 29/2017(ኢዜአ)፡-የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ በ2018 የበጀት ዓመት የተሻሻሉ አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስታወቁ።
የጤና ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የጤና ሥርዓት ኢኖቬሽንና ጥራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እንዲሁም የተያዘውን የስራ ዘመን ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በአዳማ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና አገልግሎት ጥራት፣ ደህንነት እና ፍትሃዊነትን ለማጽናት እየተሰራ ይገኛል።
በተያዘው የበጀት ዓመት ወደ ትግበራ ከሚገባባቸው ውስጥ ዋነኛው የጤና ሴክተር ሪፎርም መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ክፍተቶችን በመለየት ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት፣ ተደራሽነትንና ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ ማስቻል እንደሆነ አስረድተዋል።
የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎችና ሰራተኞች ያሉበትን ቁመና የማየት፣የመገምገምና የበለጠ በመደገፍ አቅማቸውን ማጎልበትም እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።
እንዲሁም በጤና ሥርዓት ግንባታ ሂደትም ውስብስብ ችግሮችን ቀለል አድርገን ወደ ትግባራ እንገባለን ብለዋል።
ለዚህም አስቻይ ከሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የዲጂታል መሳሪያዎች ወሳኝ መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር መቅደስ፤ በ2018 በጀት ዓመት በዲጂታላይዜሽን አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን እንተገብራለን ብለዋል።
ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት መደረጉን አስታውቀዋል።
ይህም የጤና አገልግሎቱን ቀልጣፋ በማድረግ ሕብረተሰቡን ከተላላፊና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመታደግ አጋዥ እንደሆነ አብራርተዋል።
ተወዳዳሪ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ የደረጃ መስፈርቶች ወጥተውና ጸድቀው ለትግበራ መዘጋጀታቸውንም አውስተዋል።