አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ሁነቶች አፍሪካ በኮፕ-30 የራሷን አቋም ይዛ እንድትቀርብ የሚያስችሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ሁነቶች አፍሪካ በኮፕ-30 የራሷን አቋም ይዛ እንድትቀርብ የሚያስችሉ ናቸው
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 29/2017(ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ የሚካሄዱ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ሁነቶች አፍሪካ በኮፕ-30 የራሷን አቋም ይዛ እንድትቀርብ የሚያስችሉ ሀሳቦች የሚንጸባረቁበት መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቀነስ የሚያስችል አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ቁርጠኝነቷን እያሳየች እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆየው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ይገኛል።
''ውይይቶችን ወደ ተግባርና ውጤት መቀየር” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው መርሃ ግብር፤ የአየር ንብረት ለውጥ ቃል ኪዳኖችን ወደ ሚጨበጥ የተግባር ውጤት መቀየር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ’’ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሔዎችን ማፋጠን፤ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሃሳብ የአባል ሀገራት መሪዎች በተገኙበት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመጀመሪያው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት በላቲን አሜሪካ መካሄዱን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ ግንባታ ስራ በትኩረት በመስራቷ ሁለቱን ኹነቶች እንድታስተናግድ መመረጧንም ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የጎላ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ከንግግር ያለፈ ተጨባጭ ርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቆጣጠር የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅ የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በአረንጓዴ አሻራ፣ ስንዴ ምርታማነት፣ የሌማት ትሩፋትና ታዳሽ ኃይል አማራጭ የተግባር ቁርጠኝነቷን አሳይታለች ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ የሚካሄዱት ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ስብሰባ እና የአየር ንብረት ሳምንት ለኮፕ 30 ዝግጅት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ኹነቶቹ አፍሪካ በኮፕ-30 የራሷን አቋም ይዛ እንድትቀርብ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለዋል፡፡
የዓለምን የአየር ንብረት ተፅዕኖ ለመቀነስ 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና የተገቡ ቃል ኪዳኖች ትግበራ ክፍተት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ጉዳት የሚያስተናግዱ ሀገራትንና ዜጎችን ጫና ለመቀነስ የተባበረ ትግል ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተገቡ ቃሎችና የተፈጸሙ ስምምነቶች ወደ ትግበራ እንዲቀየሩ ግፊት እንደምታደርግ ገልጸው፤ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የተግባር ርምጃዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ሳምንት ለ2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የፖሊሲ ሀሳቦችን የሚመግብና በብራዚል ቤለም ለሚካሄደው ኮፕ-30 የጋራ አጀንዳን ለመቅረጽ ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።