ቀጥታ፡

የደን ሽፋንን በማሳደግ እና የደን መጨፍጨፍ መጠንን በመቀነስ ረገድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2017(ኢዜአ)፡- የደን ሽፋንን በማሳደግ እና የደን መጨፍጨፍ መጠንን በመቀነስ ረገድ እንደሀገር አበረታች ውጤት መመዝገቡን የኢትዮጵያ ደን ልማት ገልጿል።

በኢትዮጵያ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ተጨባጭ ውጤት በማስመዝገብ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ መሆን የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።

አዲስ አበባ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ታስተናግዳለች።

የአየር ጥራትን በማሻሻል፣ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ የውኃ ምንጮች ጥበቃን በማጠናከር፣ የብዝኀ ሕይወት ብልጽግናን በማንበር፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቀነስ፣ የማኅበረሰብ ጥቅሞችን በማስፋት ብሎም የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ረገድ የደን ሚና የጎላ መሆኑ ይታመናል።

በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ሀብት ጥናት መሪ ሥራ አስፈጸሚ ብሥራት ኃይለሚካኤል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ሚና የከባቢ አየር ሚዛንን ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራን ማሳደግ እና ደኖችን በአግባቡ ማልማትና መጠበቅ ለምድርና ለሰው ልጆች ዘላቂ ሕይወት ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ነባሩን ደን በዘላቂነት ማሥተዳደር፣ የተራቆተውን የደን ገጽታ መልሶ እንዲያገግም ማድረግና ማልማት እንዲሁም አዳዲስ ደኖችን ማልማት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስቀጠል ወሳኝ ናቸው ይላሉ።

በተጨማሪም እንደዚህ ዓይነት ተግባራትን ማስቀጠል፤ የእንጨት ምርትን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር በሌሎች ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ለምሳሌ፡- እንደ ግብርና ፣ ኢነርጂ፣ ውኃ እና ቱሪዝም ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ ብሎም የብዝኀ-ሕይዎት ጥበቃን ለማስተካከል ሁነኛ መፍተሔ መሆኑን ነው የገለጹት።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የደን ሥነ-ምኅዳር አገልግሎት ማሳደግ፤ በሀብት አጠቃቀም ላይ የሚነሱ ዓለም አቀፋዊ እና አካባቢያዊ ተጽዕኖዎችን ለማስወገድ እንደሚረዳም ጠቅሰዋል።

እነዚህን ሐቆች በመገንዘብ፤ ዘላቂ የደን አያያዝ፣ የተራቆቱ የደን መልክዓ-ምድሮች ወደነበሩበት መመለስ፣ አዳዲስ ደኖችን እና የአረንጓዴ ልማት መንገዶችን በመዘርጋት በኩል የኢትዮጵያ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ቁልፍ ስለመሆናቸውም ይገልጻሉ።

ለአብነትም፤ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ ልቀት ልማት ስትራቴጂ እና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የተከለሰ የአየር ንብረት ለውጥ ዕቅድን አንስተዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራም፤ የደን ልማት እና ዘላቂ የተፋሰስ አሥተዳደር ሥራዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴን ያካተተ ጃንጥላ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አመላክተዋል።

ተቋማቸው የደን ሽፋን እና የደን ሽፋን ለውጥ መረጃ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የርቀት ዳሳሽ መሣሪያ ተጠቅሞ መረጃ ማውጣት መቻሉን ገልጸዋል።

በዚሁ መሠረትም፤ በፈረንጆቹ 2019 የደን ሽፋኑ 17 ነጥብ 2 በመቶ እንደነበር አውስተው፤ ይህ አሃዝ በ2023 ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉ ተረጋግጧል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ከፈረንጆቹ 2014 እስከ 2019 የደን መጨፍጨፍ መጠን በዓመት 38 ሺህ 194 ሔክታር ነበር ያሉት አቶ ብሥራት፤ ከ2020 እስከ 2023 ይህ አሃዝ ወደ 27 ሺህ 703 ሔክታር ዝቅ ማድረግ መቻሉን አረጋግጠዋል።

እንደሀገር እየተከናወኑ ባሉ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች በንቃት በመሳተፍ፣ በየአካባቢው ለደን ልማትና ጥበቃ ዘብ በመሆን፣ ለእጽዋትና ዛፎች በዘላቂነት ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ የደን ልማትን ማሳደግ እንደሚገባ መክረው፤ ይህ ሲሆን ሀገር እና የሰው ልጅ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚነታቸው እንደሚያድግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም