ቀጥታ፡

 "የኢትዮጵያን  ይግዙ"  ኤክስፖ ምርትን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ዕድል ፈጥሯል-ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 29/2017(ኢዜአ)፡- "የኢትዮጵያን  ይግዙ"  የንግድ ሳምንት ኤክስፖ 2017 ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ዕድል እንደፈጠረላቸው የኤክስፖው ተሳታፊዎች ገለጹ። 

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተዘጋጀው ሁለተኛው "የኢትዮጵያን  ይግዙ"  የንግድ ሳምንት ኤክስፖ 2017 መገናኛ በሚገኘው የጥራት መንደር ከነሐሴ 24 ቀነ 2017 ዓም ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

ኤክስፖው አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለገበያ እንዲያቀርቡ እንዲሁም ሻጭና ሸማቹን በማገናኘት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ ነው።

የንግድ ሳምንት ኤክስፖ ተሳታፊዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ኤክስፖው ሸማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት እንዲያገኝ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ምርትን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስርን ለመፍጠር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው፤ በዚህም ገበያውን  በማረጋጋት ቀጥተኛ የንግድ ስርዓት እንዲሳለጥ አስችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ተወካይ በሃይሉ ንጉሴ፤ ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ እህል፣ ጥራጥሬ፣ በኢንዱስትሪ የተቀነባበሩ የግብርና ምርት ውጤቶች፣ ፍራፍሬና የትምህርት መሳርያዎችን ይዞ መቅረቡን አንስተዋል።


 

ኤክስፖው በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አምራቾች የተሳተፉበት በመሆኑ ለሸማቾች የግብይት አማራጮችን እንዲያሰፋ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

ከሃማሬሳ የምግብ ዘይት ፋብሪካ የመጡት ወይዘሮ ዓለም አበበ፤ ኤክስፖው የዘይት ምርትን በፋብሪካ ዋጋ ለተጠቃሚው ለማድረስ  ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም ምርቱን በስፋት ወደ ገበያው ይዞ ለመቅረብና በዘርፉ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ነው የገለጹት። 

የአትክልት ምርት ይዞ የቀረበው ወጣት ጌዲዎን ገነቴ በበኩሉ፤ የአትክልት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች ለማቅረብ ኤክስፖው መልካም አጋጣሚን መፍጠሩን ነው የገለጸው።


 

በተለይም አምራቾችና ሸማቾች በቀጥታ ተገናኝተው ግብይት እንዲያካሄዱ የጎላ ሚና እንዳለው በመጠቆም፤ ኤክስፖው ለዋጋ ንረት መንስኤ የሆኑ ህገ-ወጥ ደላሎችና ተገቢ ያልሆነ ግብይት ማስቀረት አስችሏል ብለዋል።

በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሰማራው ዋን ኢንዱስትሪ ተወካይ ግርማ ታደሰ እንደሚሉት፤ ኤክስፖው በዘርፉ ከተሰማሩ አምራች ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስርን ለመፍጠርና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።


 

እንዲሁም በበዓል ወቅት የሚፈጠር የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና ሸማቹ የሚፈልገውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋና በቀላሉ እንዲያገኝ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

በኤክስፖው ላይ ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ አበራ አቡዬ በሰጡት አስተያየት ጤፍ፣ ጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።


 

በኤክሰፖው ላይ የቀረቡት ምርቶች ከገበያው አንጻር የዋጋ ልዩነት እንዳለው ጠቁመው፤ ይህም ሸማቹ ላልተገባ የዋጋ ጭማሪ  እንዳይዳረግ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ሸማቹ ከአምራቹ ጋር በቀጥታ የሚገናኝበት እድል መፈጠሩ ለቀጣይ የግብይት ስርአት መሳለጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በጥራት መንደር የተዘጋጀውን "የኢትዮጵያን ይግዙ" ሀገራዊ የንግድ ሳምንት ኤክስፖ ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም መርቀው መክፈታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም