ቀጥታ፡

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የእንስሳት ዝርያን የማሻሻሉ ተግባር የወተት ምርታማነትን እያሳደገ ነው

ወንዶገነት ፤ነሐሴ 29/2017(ኢዜአ)፡- በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የእንስሳት ዝርያን የማሻሻሉ ተግባር የወተት ምርታማነትን እያሳደገው መሆኑን የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በሲዳማ ክልል የ2018 በጀት ዓመት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ማስጀመሪያ ንቅናቄ በወንዶገነት ወረዳ ተካሄዷል።


 

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ እንደገለጹት በሌማት ትሩፋት በተደራጁ መንደሮች ሰው ሰራሽ የእንስሳት ዝርያን የማሻሻል ስራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል። 


 

ይህም የወተት ልማት አቅምን ማሳደጉን ገልፀው ፕሮግራሙ ሲጀመር 500 ሺህ የነበረው የወተት ላሞች ዝርያ ማሻሻል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ በማድረስ ከ2 ሚሊዮን በላይ ጥጆችን ማግኘት እንዳስቻለ ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የወተት ላሞችን ዝርያ የማሻሻል ስራ እንደሚከናወን ጠቅሰው በዚህም የሚወለዱ ጥጆችን ቁጥር ከ3 ሚሊዮን በላይ ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በእንስሳት ሃብት ልማት ረገድ እየተከናወነ ያለው ስራ የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የተጀመረውን ስራ ከማጠናከር ባለፈ ዘርፉ ለሴቶችና ወጣቶች ከፍተኛ የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በበኩላቸው በክልሉ የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከተቀረጹ ፓኬጆች ሰባቱ የእንስሳት ሃብት ልማት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የክልሉ ህዝብ በሌማት ትሩፋት በተደራጁ መንደሮች በዘርፉ በመሰማራት የወተት፣ የዶሮ፣ የማር፣ የንብና የሃር ትልን ጨምሮ በሌሎችም ተሳትፎ በማድረግ ብልጽግናን በቤተሰብ ደረጃ እንዲያረጋግጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተግባራዊ በተደረገባቸው አራት ዓመታት በእንስሳት ሃብት ልማት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን የገለጹት ደግሞ የክልሉ እንስሳት ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆምባ ናቸው።


 

በተያዘው በጀት ዓመትም የ258 ሺህ ላሞችን ዝርያ በማሻሻል ከ171 ሺህ በላይ ጥጆችን ለማግኘት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው የዛሬው መርሃ ግብርም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

በዘርፉ እየተከናወነ ያለው ተግባር የወተት ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ በመምጣቱ ለኢንዱስትሪ ፓርክና ለአዲስ አበባ ገበያ ምርቱን በብዛት በማቅረብ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተያዘው ዓመትም ህገወጥ የወተት ንግድን ለማስቀረት የሚያስችል ደንብ በማውጣት በተደራጁ መንደሮችና በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ምርትን ለገበያ የማቅረቡ ሂደት ይጠናከራል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉን ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም