ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት የትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው - አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት የትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው - አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ ፤ነሐሴ 29/2017(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ማፍራት እንዲቻል የትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ፡፡
የሲዳማ ክልል መንግስት ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ልዩ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት መርሃ-ግብር የማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በክልሉ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትን የሚያፋጥኑ ተግባራትን በመለየት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ትኩረት ከተሰጣቸው ቀዳሚ ተግባራት መካከል ትምህርት አንዱ እንደሆነ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ መፍጠር እንዲቻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ተማሪዎች ከመሠረታቸው የሚያስፈልጋቸውን በቂ ዕውቀት አግኝተው እንዲያድጉ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በሁሉም አካባቢ እንዲስፋፉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ በሁሉም ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑና ተማሪዎች በቂ ዕውቀትና ክህሎት የሚያገኙባቸው እንዲሆኑ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡
ተማሪዎቹ በቆይታቸው ያገኙት ዕውቀት ላይ ትጋትን በማከል ለመጪው ሀገር አቀፍ ፈተና ራሳቸውን ማብቃት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ2 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች በተመረጡ መምህራን ለስድስት ሳምንታት የቆየ የማጠናከሪያ ትምህርት እንደተሰጣቸው ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም በቂ ዕውቀት ማግኘታቸውንና ይበልጥ ትጋት እንዲጨምሩ የሚያደርግ ተነሳሽነትን መፍጠር እንደቻሉ ተመልክተናል ብለዋል ፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ጂሎ(ዶ/ር) በበኩላቸው ተማሪዎቹ ባለፉት ስድስት ሳምንታት በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ቆይታ ለወደፊት የተሻሉ ዜጎች እንዲሆኑና ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ የሚያዘጋጃቸውን ዕውቀት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከክልሉ መንግስት ለቀረበለት የትብብር ጥሪ በጎ ምላሽ በመስጠት የማጠናከሪያ ትምህርቱ በስኬታማነት እንዲጠናቀቅ ግብረ ኃይል በማቋቋም መስራቱንም ገልፀዋል ፡፡
ከተማሪዎቹ መካከል ከአለታ ወንዶ ወረዳ የመጣው ተማሪ አማኑኤል አዲሱ በቆይታቸው ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ብቁ እንዲሆኑ የሚረዳቸውን ዕውቀት ማግኘት እንደቻሉ ገልጿል፡፡
በመርሃ-ግብሩ ላይ የሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር አካላት፣ መምህራንና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡