የመውሊድ በዓልን በመረዳዳት በአንድነት እያከበርን ነው -የበዓሉ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመውሊድ በዓልን በመረዳዳት በአንድነት እያከበርን ነው -የበዓሉ ተሳታፊዎች
ደሴ ፤ ነሐሴ 29/2017(ኢዜአ)፡-የመውሊድን በዓል በመረዳዳት በአንድነት እያከበሩ መሆኑን በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በ"ገታ" መስጅድ የበዓሉ ተሳታፊዎች ገለፁ።
በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች 1ሺህ 500ኛው የመውሊድ በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው።
የበዓሉ ተሳታፊ ሼህ ሲራጅ መኮንን እንደገለፁት የመውሊድ በዓል የተቸገሩት የሚረዱበትና አንድነት የሚጎለብትበት ነው።
እርሳቸውም ከአዲስ አበባ ከተማ በመምጣት ታሪካዊ በሆነው ገታ መስጅድ እያከበሩ መሆናቸውን ጠቁመው በዓሉን በመረዳዳት በአንድነት እያከበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የነብዩ መሀመድ/ሰ.ዓ.ወ/ ታሪክ፣ አስተምህሮ፣ ደግነትና አዛኝነትን እየተማማርን በዓሉን ማክበር በመቻላችን ተደስቻለሁ ብለዋል።
ሌላዋ ከሸዋሮቢት ከተማ የመጡት የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ዘይባ ሁሴን በበኩላቸው ሐይማኖታዊ አስተምህሮውን ጠብቀን በዓሉን በድምቀት እያከብርን ነው ብለዋል።
"ሀገራችን ሰላም እንዲሆን፣ አንድነታችን እንዲጠናከር፣ ልማታችን እንዲቀጥል ዱዓ እያደረግን አላህን እየለመን ነው" ብለዋል።
ነብያችንንም በማውሳት አስተምህሯቸውን በማስታወስ መንገዳቸውን ለመከተል ታሪካቸውን እየተረዳን ነው ብለዋል።
"ያለንን በማካፈል፣ በመረዳዳትና አንድነታችንን በማጠናከር ነብያችንን በማስታወስ እያከበር ነው " ያለችው ደግሞ ከደሴ ከተማ የመጣችው ወጣት ሂክማ ሀሰን ናት።
ወጣት እስማኤል አህመድ በበኩሉ ከተለያየ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመምጣት ተሰባስበን የመውሊድ በዓል ማክበራችን አንድነታችንን ለማጠናከርና ለመተዋወቅ እድል ፈጥሮልናል ብሏል።
የ"ገታ" መስጅድ ምክትል አስተዳዳሪ ሸህ ኡማድ ሐጅ ሙሄዲን እንደገለጹት ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ምዕምናን የመውሊድን በዓል በድምቀት እያከበሩ ነው ብለዋል።
በበዓሉ ምዕምናኑ የነብዩ አስተምህሮትን እንዲገነዘብ ከማድረግ ባለፈ ስለ ሀገር ሰላምና አንድነትም ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ ሀይሉ ታደሰ በበኩላቸው በዓሉ በሁሉም ወረዳዎች በድምቀት እየተከበረ መሆኑን አስታውቀዋል።