የግድቡ መጠናቀቅ ለዘመናት ለቆየው የኢትዮጵያዊያን የመልማት ቁጭት ምላሽ ያስገኘ ነው - የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ መጠናቀቅ ለዘመናት ለቆየው የኢትዮጵያዊያን የመልማት ቁጭት ምላሽ ያስገኘ ነው - የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች

ቦንጋ፤ነሐሴ 29/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለዘመናት ለቆየዉ የኢትዮጵያዊያን የመልማትና የማደግ ቁጭት ምላሽ ያስገኘ ነው ሲሉ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ዓባይ ባለመገደቡ ለዘመናት ቁጭት ውስጥ ገብተው የቆዩ ኢትዮጵያዊያን የህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ አሻራቸውን እያሳረፉ የሚጠናቀቅበትን ቀን በተስፋ ሲጠባበቁ ቆይተዋል።
ይህ የኢትዮጵያዊያን ተስፋ ፍሬ አፍርቶ ግድቡ በበርካታ ውጣ ውረዶችና ፈተናዎች ዉስጥ አልፎ በመንግስት ቁርጠኛ አመራርና በህዝቦች የተባበረ ክንድ እነሆ ከዳር መድረሱ ተበስሯል።
ጉዳዩን አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፥ ግድቡ በመጠናቀቁ ለዘመናት በቁጭት ውስጥ የቆየዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምላሽ አግኝቷል።
የህዳሴ ግድብ ሲጀመር በታላቅ ደስታ ዉስጥ እንደነበሩ የተናገሩት መምህርት ወይነሽት ጫኔ፣ መንግስት በወሰደው በሳል እርምጃና ባሳየዉ ቁርጠኛነት ለፍፃሚ መብቃቱ ዳግም ከመወለድ አይተናነስም ብለዋል።
ያለማንም እርዳታ በራሳችን የተባበረ ክንድ የሰራነው ፕሮጀክት መሆኑ ደግሞ አንድ ከሆንን የማንችለው ነገር፤ የማናልፈው ፈተና እንደሌለ ማሳያ ነው ሲሉም ጠቁመዋል።
"ግድቡ የሀገራችን የብልፅግና መሰረት ነው" ያሉት ሌላኛው የከተማው ነዋሪ መምህር ተክሌ ገረመው፣ ቦንድ በመግዛት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ግድቡ የህብረት ውጤት፣ የይቻላል ምልክት እንዲሁም የሀገራችን ኩራት ነው" ያሉት መምህር ተክሌ፣ ይህም ከተደመርንና ከተጣመርን ኢትዮጵያን ከድህነት ማውጣት እንደምንችል አቅም የሚሆነን የጋራ ሀብታችን ነው ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በማየታቸው እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ትልቅ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው የጠቆሙት የከተማው ነዋሪ አቶ ኬሮ ገሬናም ግድቡ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ዘመን ማብሰሪያ እንደሆነም ገልፀዋል።
ይህ ትውልድ ተሻጋሪ የሆነው ፕሮጀክት "የዘመናችን ዓድዋ፣ የአንድነታችን ምስጢር ነው" ያሉት አቶ ኬሮ፣ ሀገራችን በዓለም አደባባይ ደምቃ የምትታይበት፤ ታሪኳንም የምታድስበት ትልቁ ሀብታችን ነው ብለዋል።
"የዚህ ታሪክ ሰሪ ትውልድ አካል በመሆኔ እድለኛ ነኝ" ያለው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ፍቅሩ በላይ፣ለድህነትና ችግር እጅ ሳንሰጥ ተባብረን ግድቡን ከዳር ማድረስ መቻላችን አይችሉም ሲሉ ለነበሩ አካላት የኢትዮጵያን ልክ ያሳየ መሆኑን ተናግሯል።
ከተባበርንና ለሀገር ጥቅም በአንድነት ከቆምን ግድቡን በራሳችን አቅም ጀምረን እንደጨረስነው ሁሉ ቀጣይም ሌሎች ፕሮጀክቶችን እና የልማት ስራዎችን የማሳካት አቅምና ብቃት እንዳለን ትምህርት ያገኘንበት ነውም ብሏል።
ለግድቡ ግንባታ ያሳየነውን ሕብረትና አንድነት በሌሎች የልማትና የሰላም ስራዎች ላይ በመድገም የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻችንን እንወጣልን ሲሉም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።