የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2017(ኢዜአ)፦ የ2025/26 የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ዞን ማጣሪያ ዛሬ በኬንያ ይጀመራል።
በውድድሩ ላይ ዘጠኝ ሀገራት በሶስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።
ኢትዮጵያን በሴካፋ ዞን ወክሎ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በምድብ ሁለት ከብሩንዲው ቶፕ ገርልስ አካዳሚ እና ከሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ ተደልድሏል።
በውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ ጋር ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት በንያዮ ስታዲየም ያደርጋል።
ሁለቱ ቡድኖች በ2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የ2024/25 የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በተመሳሳይ በመክፈቻ ጨዋታ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል።
ንግድ ባንክ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።
በብርሃኑ ግዛው የሚመራው ቡድን በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሲሳተፍ የዘንድሮው ለአምስተኛ ተከታታይ ዓመት ነው።
ክለቡ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው አራት ተሳትፎዎች በ2016 ዓ.ም የሴካፋ ዞን ማጣሪያን በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉ የሚታወስ ነው።
የሴካፋ ዞን ማጣሪያ እስከ መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ማጣሪያውን የሚያልፍ ክለብ ሴካፋን ወክሎ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።