ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መፈፀም የምንችል ህዝቦች መሆናችንን በተግባር ያሳየንበት ነው-የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች

ሰመራ፣ነሐሴ 29/2017 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መፈፀም የምንችል ህዝቦች መሆናችንን በተግባር ያሳየንበት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የህዳሴ ግድብን በስኬት መጠናቀቅ ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት "እኛ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ጀምረን መጨረስ የሚቻለን መሆኑን ያስመሰከርንበት ነው"።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ግርማ ሃጎስ፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመቻል፣ የመፈፀምና ያለምነውን የማሳካት አቅማችንን ያሳየንበት ነው ብለዋል።

ግድቡ ያለመሸነፍን ያረጋገጥንበትና ሀገራችን የጀመረችውን ውጥን የመጨረስ አቅምን በተግባር ያስመሰከረችበት ነው ብለዋል።

መላው ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆንና በህብረት ከቆምን ማሸነፍና ማሳካት እንደሚቻለን አሳይተናል ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አድናን ሁሴን ናቸው።

ፕሮጀክቱ ሀገራችንን ወደ ብልፅግና ማማ ማሻገር የሚያስችልና እንደ ተዓምር ሊገለፅ የሚችል የዚህ ዘመን ትውልድ ውጤት መሆኑን ነው የተናገሩት።

አቶ ያሲን አህመድ በበኩላቸው፥ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደማችንና የላብ አሻራችን የታተመበት የመቻል አቅማችን የተንፀባረቀበት ፕሮጀክት ነው።

በርካታ ፕሮጀክቶችን በመፈፀም ማሳካት የቻልንበትና የይቻለናል መንፈስ እንዲጎለብት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ከማንም ሳንጠብቅ በራሳችን አቅም ጀምረን መጨረስ እንደሚቻለን ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም