ቀጥታ፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ልማት ቁርጠኝነት ያሳየ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው - ጀምስ ሙሮምቤዚ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2017 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ልማት የፖሊሲና የተግባር ቁርጠኝነትን በተጨባጭ ያሳየ የንፁህ ኢነርጂ ማመንጫ ፕሮጀክት መሆኑን በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአየር ንብረት ፖሊሲ ማዕከል ኃላፊ ጀምስ ሙሮምቤዚ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአፍሪካ የአየር ንብረት ፖሊሲ ማዕከል የአየር ሁኔታ ምልከታ ስርዓቶች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት መረጃን እንዲተነትኑ እና ውጤታማ የአየር ንብረት ነክ ፖሊሲዎችን፣ ስልቶችን እና እቅዶችን እንዲያዘጋጁ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ ስላለው ተጽዕኖ ሰፊ ምርምር በማድረግ በአህጉሪቷ የሚገኙ መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ አጋዥ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ጫናዎችን እያስከተለ ቢሆንም መፍትሔ መስጠት የሚያስችሉ ዕድሎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሥርዓተ ምህዳር፣ የታዳሽ የኃይል ምንጮች እና እንደ ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ተነሳሽነቶች ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ እና የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ወሳኝ አቅሞች ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በማረጋገጥ የበካይ ጋዝ ልቀትን እየተከላከለች እንደምትገኝ አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ስርዓት ለመገንባት ጉልህ አበርክቶ ያለው ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ንጹህ ኃይል በማመንጨት ሀገሪቱን ከነዳጅ አጠቃቀም እንድትወጣ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፥ ከህዳሴው ግድብ የሚመነጨው ኃይል ለአረንጓዴ ልማት መሳካት አይተኬ ሚና አለው ብለዋል።

ሀገሪቱ ለአረንጓዴ ትራንስፖርት በሰጠችው ትኩረት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት መጠቀም መጀመሯን አድንቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም