ማህበሩ ወደ ህብረተሰቡ በመውረድ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን አስከፊነት በማስተማር ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ወደ ህብረተሰቡ በመውረድ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን አስከፊነት በማስተማር ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው
አሶሳ፤ነሐሴ 28/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ወደ ህብረተሰቡ በመውረድ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን አስከፊነት በማስተማር ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በክልሉ አቡራሞና ኡራ ወረዳዎች ላይ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ዙሪያ በተከታታይ ሲሰጥ በነበረው ስልጠና በወረዳዎቹ የመጣውን ለውጥ አስመልክቶ የመስክ ምልከታ አካሂዷል።
በምልከታው ወቅት የተገኙት የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ፤ በክልሉ የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ በሴቶች ህይወት ላይ ከፍተኛ የስነ ልቦና እና የአካል ጉዳት የሚያደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ይስተዋሉ ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት፥ ወደ ህብረተሰቡ በመውረድ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን አስከፊነት በማስተማር ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ቢሯቸው ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ጋር በመተባበር በሌሎች አካባቢዎች በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሞገስ ነገሮ በበኩላቸው፥ ማህበሩ ሰብአዊነትን በማስቀደም በሴቶች ላይ የሚደርሱ የአካልና የስነ ልቦና ጉዳትን ለመቀነስ እየሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ አቡራሞና ኡራ ወረዳዎች ላይ ህብረተሰቡን በማስተማር በአሁኑ ሰዓት ያለዕድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ጨምሮ ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በራሳቸው ተነሳሽነት እንዲከላከሉ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
በኡራ ወረዳ አቁዳ ቱመት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ፋጡማ ሙሳ እንደተናገሩት፥ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አስከፊነት ዙሪያ ማህበሩ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንደሰጣቸው ገልጸዋል።
በዚህም በቀበሌው በአሁኑ ሰዓት የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለዕድሜ ጋብቻ እንደማይፈጸም አረጋግጠዋል።
ሌላዋ የአቡራሞ ወረዳ ነዋሪ ሀጂጄ ሀሊፋ በበኩላቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶች ህይወት ላይ አላስፈላጊ ጫና የሚያመጣ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።
ጽህፈት ቤቱ በፈጠረላቸው ግንዛቤ መሠረት የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለዕድሜ ጋብቻ በሴቶች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት መከላከል እንደሚገባቸው ለሌሎች ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውንም አክለዋል።