ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጠንካራ ክንዳቸው እውን ያደረጉት ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት ነው - ኡስታዝ ጀማል በሽር - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጠንካራ ክንዳቸው እውን ያደረጉት ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት ነው - ኡስታዝ ጀማል በሽር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ጠንካራ ክንዳቸው እውን ያደረጉት ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት መሆኑን “የዓባይ ንጉሶች” ሚዲያ ባለቤትና ስለህዳሴ ግድብ በሚዲያቸው በአመክንዮ የሚከራከሩት ኡስታዝ ጀማል በሽር ገለጹ።
ኡስታዝ ጀማል በሽር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከግንባታ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ድሎችና ስኬቶች የተገኙበት መሆኑን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ግድቡ ድህነትን የማሸነፍ ጉዞ ጅማሮን ያበሰረ መሆኑንም አመልክተዋል።
ህዳሴ ኢትዮጵያዊያን ላባቸውን፣ ደማቸውንና ገንዘባቸውን በማፍሰስ ያሳኩት የህዝብ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቶቿ የመጠቀም እና የመልማት ፍትሐዊ መብቷን በተግባር ያሳያችበት ነው ብለዋል።
ህዳሴ ግድብ ኢ-ፍትሐዊ የቅኝ ግዛት ውሎችን ዋጋ ቢስ በማድረግ አዲስ የትብብር ምዕራፍን በተፋሰሱ ሀገራት መካከል መፍጠሩንም ነው ያስረዱት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ የ“ኩስመና ታሪክ ማብቂያ” በሚል ርዕስ በተካሄደው የጉባ ላይ ወግ የሰጡትን ማብራሪያ እንደተከታተሉ የገለጹት ኡስታዝ ጀማል፥ የህዳሴ ግድብ ስኬት የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ቁጭት እውን ያደረገ መሆኑን በተጨባጭ የተገነዘብንበት ነው ብለዋል።
ኡስታዝ ጀማል እንደጠቀሱት ኢትዮጵያውያን በተባበረ ጠንካራ ክንዳቸው ታሪክ ቀያሪ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እንዲጠናቀቅ ማስቻላቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ግድቡ በቀጣይ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ለማሳካት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት።
ህዳሴ ጅማሮ ነው ያሉት ኡስታዝ ጀማል ኢትዮጵያ በቀጣይ የውሃ ሀብቶቿን በመጠቀም ግድቦችን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማፋጠን ሁለንተናዊ እድገቷን እንደምታረጋገጥ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያዊያን በህዳሴ ግድቡ የአሳ ምርትን ጨምሮ ሌሎች ለሀገር ብልጽግና የሚበጁ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል፡፡
ግድቡ ከኤሌትሪክ ኃይል ማመንጨት ባለፈ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጉልበት ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያዊያን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሳዩትን ህብረት በሌሎችም የጋራ ጉዳዮች ላይ በማስቀጠል ሀገራቸውን ለማልማት አበክረው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።