ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድሩ ለኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ትልቅ ሚና ይጫወታል-ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድሩ ለኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ትልቅ ሚና ይጫወታል-ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 28/2017(ኢዜአ)፦ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድሩ ለኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ፡፡
ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድር የመክፈቻ ስነስርዓት "ጥበባት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ከኢትዮጵያ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ እስከ ብሔራዊ ቴአትር የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ የጎዳና ላይ ትርኢቶች ቀርበዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚሁ ወቅት፥መንግስት ከምንጊዜውም በላይ ለኪነ-ጥበብ ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመዲናዋ እና በክልል ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የኮሪደር ልማት ወጣቶችን ታሳቢ በማድረግ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራና የኪነ ጥበብ ቦታዎች በስፋት መገንባታቸውን አንስተዋል።
ይህም ወጣቶች ተሰጥኦዋቸውን አውጥተው ለመጠቀም ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የኢትዮጵያን ማንሰራራት ለማብሰር ትልቅ አቅም እንዳላቸው ጠቁመው፥ ፍቅርን አንድነትንና መተሳሰብን የሚያጠናክሩ ጥበባትን ማጉላት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድሩ ሀገራዊ ትርክት ግንባታን በማጉላት ለኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ነው ያነሱት፡፡
መጪው አዲስ ዓመት ኢትዮጵያ ህልሞቿን ወደ ተጨባጭ ምዕራፍ የምታሸጋግርበት መሆኑን የገለጹት አማካሪ ሚኒስትሩ፣ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ዓባይን ጨምሮ በሀገራዊ ጉዳዮች ከወቀሳ ወደ ሙገሳ መሸጋገራቸው ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በየአካባቢው ያለውን የኪነጥበብ አቅም በማውጣት ለትውልድ ቀረጻና ለጠንካራ ሀገር ግንባታ መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፥ የጥበብ ውድድሩ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የጥበብ አቅም አጉልቶ ለማሳየት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ጥበብ የሀገርን ገፅታ ለመገንባት ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚከናወኑ የኮሪደር ልማቶች ለኪነ-ጥበብ ሥራዎች የበለጠ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩም አንስተዋል።
ውድድሩ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2017 የሚቆይ ሲሆን ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ሲሆን በብሔራዊ ቴአትር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጓዥ ተውኔት እንደሚቀርብም ጠቁመዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው፥ ውድድሩ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉበት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ማንሰራራት የሚበሰርበት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚመረቅበት ወቅት በመሆኑ በመድረኩ የሚቀርቡ የጥበብ ስራዎች ከግድቡ ጋር ተያያዥነት ያላቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም፥ ህዳሴ ግድብ ብርሃን ሲያመነጭ የጥበብ ባለሙያው ደግሞ በጥበብ ወዝ፣ ለዛ፣ አንደበት እንዲሁም ክዋኔ በመጠቀም ብስራቱን ለህዝብ ያደርሳል ብለዋል።