ቀጥታ፡

ብቁ የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮችን ማፍራት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እየተፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2017(ኢዜአ)፦ብቁና ተወዳዳሪ የሂሳብ ባለሙያዎች እና ኦዲተሮችን ማፍራት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ አጎናፍር ገለጹ።

አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚደረግባት ሀገር ናት።

የተቋማት ቁመና የሚገመገመው በሚያቀርቡት ፋይናንሻል ሪፖርት መሆኑን ጠቁመው፥ ሪፖርቱ የሚዘጋጀው በዓለም አቀፍ የሂሳብ አያያዝ መስፈርት መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እነዚህን የሂሳብ መስፈርቶች ተቀብላ እየተገበረች መሆኑን ገልጸው ቦርዱ ተፈጻሚነቱን እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ቦርዱ በዋናነት የባንኮች፣ የኢንሹራንሶች እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የፋይናንሺያል ሪፖርቶችን በስታንዳርድ መሰረት መዘጋጀታቸውን እንደሚፈትሽ አንስተዋል።

በፋይናንሺያል ሪፖርት እና ኦዲት ሪፖርት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ባለሙያው መሆኑን ገልጸው እንደ ሀገር ያሉ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ገበያው የሚፈልገው የባለሙያ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት፥ ይህንን ከትምህርት ስርዓቱ ጋር ማጣጣም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ቦርዱ የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን በማንሳት፥ በዘላቂነት ቦርዱ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት በአዋጅ መቋቋሙን አመላክተዋል።

ግዙፍ ኢኮኖሚ እና ትልቅ ህዝብ ላላት ኢትዮጵያ ብቁና ተወዳዳሪ የሂሳብ ባለሙያዎችን በቀጣይነት ለማፍራት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

በኢንሹራንሶች አካባቢ አንዳንድ የፋይናንስ ሪፖርት ስራዎች ወደ ውጭ ሀገራት ተልከው ይዘጋጁ እንደነበር በማውሳት፥ ኢንስቲትዩቱ እነዚህን ችግሮች ሙሉ በሙሉ መፍታት የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በሚፈጥረው የባለሙያዎች ዝውውር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ከታህሳስ ወር ጀምሮ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም