ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ አስፈላጊውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 28/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ አስፈላጊውን የገንዘብና ሙያዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለፀ።

የህዳሴ ግድብ ምርቃትን ምክንያት በማድረግ ጳጉሜን 2 በሁሉም ሚሲዮኖች ድጋፍ ላደረጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን  ምስጋና የማቅረቢያ መርሐ ግብር እንደሚካሄድም ተገልጿል።  

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራስ አቅም እውን ለማድረግ ጥሪ ከቀረበበት ግዜ አንስቶ ህብረተሰቡ በገንዘብ ፣በጉልበትና በአይነት ድጋፍ በማድረግ አለኝታነቱን አሳይቷል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ የኑሮ መደብ ሳይገድበው እናቶች ከመቀነታቸው ፈተው፣ ባለሃብቱ ሃብቱን አጋርቶ ምሁራን እውቀታቸውን አፍስሰው በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ግንባታው ተጠናቆ በቅርቡ እንደሚመረቅ ተበስሯል።

ለግድቡ ግንባታ በአገር ውስጥ ካለው ህብረተሰብ በተጨማሪ በመላው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ድንበር ሳይገድባቸው አስተዋፅኦ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ ለኢዜአ እንዳሉት ዳያስፖራው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ በተለይ ምሁራን ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ባከበረ መልኩ ግድቡን መገንባቷን በማስገንዘብ በኩል የበኩላቸውን ሚና ሲወጡ መቆየታቸውን ገልፀዋል። 

አገልግሎቱ በተለያዩ አገራት ካሉ ሚሲዮኖች ጋር በመቀናጀት ከመጋቢት እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም ድረስ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ማካሄዱን ተናግረዋል። 

በመርሃ ግብሩ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በልገሳና በቦንድ ሁለት ሚሊየን ዶላር መገኘቱን አስታውሰው በሐምሌ ወር 2017 ብቻ 200 ሺህ ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል። 

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምርቃትን ምክንያት በማድረግ ጷጉሜን 2 ቀን 2017 በሁሉም ሚሲዮኖች ድጋፍ ላደረጉ አካላት የምስጋና መርሃ ግብር እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም