ትልቅ የሀገር ሀብት የሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን አስደስቶናል - ኢዜአ አማርኛ
ትልቅ የሀገር ሀብት የሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን አስደስቶናል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 28/2017(ኢዜአ)፦ለትውልዱ ትልቅ የሀገር ሀብት የሆነውንና የበኩላችንን አሻራ ያሳረፍንበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን አስደስቶናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያውያን የማንሰራራት ተስፋ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመላው ኢትዮጵያዊ ትብብር እውን ሆኗል፡፡
የግድቡ ግንባታ ከተበሰረበት ጊዜ አንስቶ በተለያየ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለግንባታው ያልተቋረጠ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
እናቶችም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መቀነታቸውን ፈትተው ያልተቋረጠ ድጋፍ አበርክተዋል፡፡
ከነዚህ መካከል በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የተለያዩ ምርቶችን በመሸጥ የሚተዳደሩ እናቶች ይገኙበታል።
በሶስት ማህበር ተደራጅተው የሚሰሩት 48 እናቶች ለአንድ ዓላማ በጋራ በመቆም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ድረስ በሚችሉት አቅም በተለያዪ ጊዜያት ድጋፍ አድርገዋል።
የተባብረን እንደግ ማህበር ጸሀፊ ወይዘሮ ዘይነባ አርጋው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በሀገር አቅም መገንባት ከተጀመበረት ጊዜ አንስቶ የፕሮጀክቱን ፍጻሜ ማየት የሁልጊዜ ህልማቸው እንደነበረ ገልጸዋል።
ለፕሮጀክቱ ግንባታ በሶስት ማህበራት ተከፋፍለን በተለያየ ንግድ ላይ ተሰማርተን የምንገኝ 48 ሴቶች የቦንድ ስጦታ ስናደርግ ቆይተናል ብለዋል።
የተባብረን እንደግ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ እንሴኔ ጀቤሳ በበኩላቸው ለግድቡ እውን መሆን ከጅማሮው አንስቶ አቅማቸው የፈቀደውን ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የፍቅር ይስጠን ማህበር ገንዘብ ያዥ ወይዘሮ መስከረም ከበደ ኢትዮጵያውያን "እንደጀመርን እንጨርሰዋለን!" በሚል ቁርጠኝነት የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቃችን ልማቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን በራስ አቅም መጨረስ እንደምንችል ያሳየንበት ነው ብለዋል።
መንግስት ለሀገር እድገት በሚሰራቸው የልማት ስራዎች ለመሳተፍ ሁሌም ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የስራ በፍቅር ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ምስራቅ ገብረየስ ናቸው፡፡
አስተያየት ሰጪዎች የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እና ለነገ ሀገር ተረካቢ ልጆቻችን የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ እድል የፈጠረ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ ህዳሴ ግድብን በራስ አቅም መገንባትና ማጠናቀቅ እንደቻልነው ሁሉ መንግስት በሚሰራቸው ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ በመሆን የሚጠበቅበንን ሚና ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የዓላማ ጽናትን ካጎለበትን ከእድገት ጎዳና ወደ ኋላ የሚመልሰን ምንም ነገር አይኖርም ሲሉ ገልጸዋል።
ሁሉም ዜጋ በተለያየ መንገድ ድጋፍ በማድረግ ያሳየው ትብብር ኢትዮጵያዊያን ለመልማት ያላቸውን ፍላጎት በተግባር ያሳዩበት ነው ብለዋል።