የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ እና የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቃል ኪዳን - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ እና የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቃል ኪዳን
የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖዎች በአፍሪካ ምድር መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ከተከታታይ የድርቅ ክስተቶች እስከ አውዳሚ የጎርፍ አደጋዎች አህጉሪቷ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈተነች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥ የአፍሪካ አረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆና መጥታለች።
በአዲስ አበባ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ስትራቴጂዋን የምታጋራበትና አፍሪካ ለችግሩ የተግባር ምላሽ እንድሰጥ የማስተባበር ሚናዋን የምትወጣበት ነው።
ከጉባኤው መሪ ሀሳቦች መካከል “ አረንጓዴ ተኮር ወይይቶች እና አረንጓዴ የተግባር ምላሾች” አንዱ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ያላትን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ቁርጠኝነት የበለጠ ያስተጋባል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች ከወረቀት አልፎ በእግራቸው እንዲራመዱ ለማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ ስራዎችን እያከናወነች ይገኛል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ህልም፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ
እ.አ.አ በ2011 ይፋ የሆነው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ከኢኮኖሚ እድገት ጎን ለጎን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር እና ከካርቦን ነጻ የሆነ ኢኮኖሚን የመገንባት ውጥን ያለው ነው።
ስትራቴጂው አራት አንኳር ምሰሶዎች አሉት።
የመጀመሪያው ዘላቂ ግብርና እና የቁም እንስሳት ተጠቃሚነትን ማሳደግ ሲሆን በዚህ ውስጥ ምርማነትን መጨመር፣ የአርሶ አደሮችን ገቢ መጨመር፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ብክለትን መቀነስ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
በደን እና ደን መልሶ ልማት አማካኝነት ለደኖች ጥበቃ ማድረግ፣ የደን መልሶ ልማት እና ካርቦንን አምቆ መያዝ የሚያስችሉ ግዙፍ አረንጓዴ ፕሮጀክቶችን ወደ ትግበራ ማስገባት ሁለተኛው ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ነው።
የሃይድሮ ፓወር፣ እንፋሎት፣ ነፋስ እና ፀሐይን በመጠቀም የታዳሽ ኃይል ምንጭን ማስፋት ሌላኛው የትኩረት ማዕከል መሆኑን በስትራቴጂክ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
በትራንስፖርት፣ በኢንዱስትሪና በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ዘመናዊ እና ኃይል ቆጣቢ የቴክኖሎጂ አማራጮችን መጠቀም አራተኛው ጉዳይ ነው።
በስትራቴጂው እና በተግባር ምላሽ ጥምርታ የተገኙ ቁልፍ ስኬቶች
አረንጓዴ አሻራ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትልቁ የተግባር ማሳያ የሚሆን ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ እስከ አሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
አረንጓዴ አካባቢ ጥበቃ ስራ ባለፈ የማህበረሰብን ተሳትፎ በግልጽ ያሳየ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።
ኢትዮጵያ 96 በመቶ የኃይል ምንጯን ከታዳሽ ኃይል ምንጭ እያገኘች መሆኗ የስትራቴጂው ስኬታማነት አመላካች ነው ማለት ይቻላል።
ብዝሃ የኢነርጂ አማራጮችን መጠቀም ከብክለት ነጻ የኃይል አቅርቦት እንዲገኝ እያደረገ ነው።
በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ አማካኝነት የተዘጋጀው የፋይናንስ ማዕቀፍ በገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት የሚመራ ነው። በሚኒስቴሩ አማካኝነት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና የማጣጣሚያ ፕሮጀክቶችን መተግበር የሚያስችሉ ሀብቶችን ማሰባሰብ ችሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም እና አረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ፈንዶች የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቷል።
የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፤ የአረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን አቀጣጣይ ሞተር
ጉባኤው የሀገራት መሪዎች፣ የአየር ንብረት ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮች እና የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ነው።
ባለድርሻ አካላቱ የአፍሪካን ሀገር በቀል መፍትሄዎች በላቀ ሁኔታ መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ የአረንጓዴ ለውጥ ስራ በተሞክሮነት ይቀርባል።
ከአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ጋር የተጣጠሙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ከውጭ እርዳታ ይልቅ ዘላቂነት ባለው ሀገር በቀል ስራ ማስፋት እና መተግበር ሌላኛው አጽንኦት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ማጠቃለያ
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትውልድን የሚሻገር ሁሉን አቀፍ እሳቤ ነው።
ስትራቴጂው የኢኮኖሚ እድገትን ከአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና ብክለትን ቅነሳ እጅ ለእጅ አያይዟል።
ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ የሚካሄደው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ራዕይ ለአፍሪካ የተነሳሽነት ምንጭ እየሆነ ባለበት ወቅት ነው።
በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ከመትከል እስከ የታዳሽ የኃይል ምንጭን ማስፋት ኢትዮጵያ አረንጓዴነትን በንግግር ሳይሆን በተግባር ገልጣ እያሳየች ትገኛለች።
ይህ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ህዳሴ አፍሪካውያንና የተቀረው ዓለም ሊከተሉት የሚገባ መልካም ተግባር ነው።