የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ሌላ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም እውን ለማድረግ የሚያነሳሳ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ሌላ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም እውን ለማድረግ የሚያነሳሳ ነው
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 28/2017 (ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ትውልዱ ሌላ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም እውን እንዲያደርግ የሚያነሳሳ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ገለፀ።
የማሕበሩ ፕሬዚዳንትና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት አባል ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፥የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን የኢትዮጵያዊያንን የዘመናት ቁጭት የፈታ ነው።
ትውልዱ ከውጭና ከውስጥ የሚደርስበትን ጫና ተቋቁሞ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ መቻሉ ትልቅ የጀግንነት ታሪክ መሆኑን ተናግረዋል።
የግንባታው መጠናቀቅ ለቀጣዩ ትውልድ ከንድፈ ሐሳብ የተሻገረ የተግባር ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነም አስታውቀዋል።
አዲሱ ትውልድ በቀጣይ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን እንዲያደርግ፣የተገነቡ ሃብቶችን በአግባቡ እንዲጠቀምና እንዲንከባከብ እድል የሚፈጥረ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ ለነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማንኛውም አይነት ጫና ቢገጥሙት በትብብር በመስራት ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በቀጣይ ያለምንም የውጭ ድጋፍና እርዳታ በራሷ አቅም ከድሕነት ለመውጣት የጀመረችውን ጉዞ ማሳካት እንደምትችል የሚያመላክት መሆኑን አንስተዋል።
የግድቡ ግንባታ ከሃይል አቅርቦት በተጨማሪ በሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ብልጽግና በማረጋገጥ ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሳየውን ህብረት እና አንድነት በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ለመድገም መረባረብ ይጠበቅበታል ብለዋል።