መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችል ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችል ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 28/2017 (ኢዜአ)፦መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችል ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ አስገነዘቡ።
ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የአየር ንብረት ለውጥ የሰዎችን ህይወት በማጎሳቆልና መሰረተ ልማቶችን በማውደም መጠነ ሰፊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
የፓሪስ ስምምነት ከተፈረመ ከአሥር ዓመታት በላይ ቢሆነውም በአግባቡ እየተተገበረ አለመሆኑን ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ግምገማ አስከፊ እውነታዎችን ማረጋገጡን ጠቁመው፥ በዚህም የፓሪሱን ስምምነት ቃል ለመጠበቅ፣ ፍትሕዊና ዘላቂ ደህንነቱ የተጠበቀ ዓለምን ለመገንባት ደፋርና ለውጥ አምጪ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠይቃል ብለዋል።
አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ያላት ድርሻ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም አስከፊ ተጽዕኖ እየተጋፈጠች እንደምትገኝ አስረድተዋል።
በመሆኑም በአህጉሪቱ ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ ልማትን ማፋጠን፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የምግብ ዋስትናን ማሻሻልና ሁለንተናዊ የኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
አፍሪካ የተፈጥሮ ሃብቷን ሙሉ በሙሉ ለሕዝቦቿ ጥቅም ያላዋለችና ለቀጣይ ዕድገቷም ጠንካራ ምኞትና አዲስ ተስፋ ያላት አህጉር መሆኗን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ ሥርዓት እየገነባች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ በታዳሽ ኃይልና በኮሪደር ልማት የዜጎችን ህይወት የሚቀይሩ፣ ዘላቂና ምቹ አካባቢን የሚፈጥሩ፣ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ዓለም አቀፋዊና መፍትሔውም የእያንዳንዱ ሀገር የተግባር ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተዋል።
መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል ደፋር እርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ እንዳሉት፥ አፍሪካ ሁለተኛውን አህጉራዊ የአየር ንብረት ጉባኤ በመጪው ሳምንት ለማካሄድ ተዘጋጅታለች ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተነች የምትገኘው አፍሪካ ድምጿ ጎላ ብሎ እንዲሰማና ምላሽ እንዲያገኝ በጋራ መነሳት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአየር ንብረት ፋይናንስ ፍትሐዊነት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለአቅም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ከአፍሪካ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአየር ንብረት ሳምንትና ጉባኤ ከቃል ባለፈ ስኬታማ ድርድርና የተግባር እርምጃን ለመውሰድ ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግል አብራርተዋል።
መድረኩም ምኞት ከተግባር ጋር የሚገናኝበት፣ የተገቡ ቃሎች ወደ ተግባር የሚለወጡበት፣ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚቀየስበት፣ ዘላቂ ልማትን የሚያጎለብቱ ሀሳቦች የሚፈልቁበት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከአየር ንብረት ጋር ተስማሚ በሆነ መልኩ እየተተገበረ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት ምክትል ዋና ጸሐፊ ኑራ ሀመላዲጂ፤ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የአፍሪካ ነፃነትና የዲፕሎማሲ ምልክት ሆና ቀጥላለች ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ቀውስን ያለ ትብብር ማሸነፍ አይቻልም ያሉት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ፤ የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት ለማስመዘገብ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
እ.አ.አ. እስከ 2035 ድረስ ለታዳጊ ሀገራት የሚደረገውን የፋይናንስ ፍሰት በየዓመቱ ወደ አንድ ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማሳደግ የተገባው ቃል በተግባር እንዲፈጸም መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።